ኢትዮጵያ በጣም ዝቅተኛ ከሆነው ዳናኪል ሸለቆ አስከ ባሌ እና ሰሜን ተራሮች ያሉ ከፍታዎች፣ ከላሊበላ እስከ አክሱም ያሉ የቀደምት ኢትዮጵያውያን ጥበብ መገለጫዎች፣ ምሥጢራዊዎቹ የጢያ ትክል ድንጋዮች ያሉ ልዩ የተፈጥሮ፣ የባህል እና ታሪካዊ ቦታዎችን የታደለች የውበት ባለፀጋ ናት።
ኢትዮጵያ 12 የሚዳሰሱ እና 7 የማይዳሰሱ ቅርሶችን በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ያስመዘገበች ሲሆን፣ ይህ ቁጥር ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገራት አንዷ ያደርጋታል።
ይህን ሁሉ ሀብት የያዘችው ኢትዮጵያ ግን ሀብቷን ለብልጽግናዋ ሳትጠቀም ቆይታለች። ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ ግን ይህ አካሄድ ተለውጦ የቱሪዝም ዘርፉ ከኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ምሰሶዎች አንዱ ሆኖ እየተሠራበት ነው።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በፈንጆቹ 2023/24 ኢትዮጵያ 1.48 ሚሊዮን ቱሪስቶችን አስተናግዳ 4.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘች ሲሆን፣ ይህ ገቢ ከዚያ በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል።
ይህ ዕድገት የመጣው መንግሥት ቱሪዝምን አንዱ የኢኮኖሚ ምሰሶ አድርጎ ከመውሰዱም በላይ በሠራቸው ተጨባጭ ሥራዎች ነው።
በገበታ ለሸገር የተሠሩ እንደ አንድነት ፓርክ፣ የወዳጅነት ፓርክ ያሉ እንዲሁም በገበታ ለሀገር የተሠሩ እንደ ወንጪ ኢኮ ቱሪዝም ሎጅ፣ ጎርጎራ እና ጨበራ ጩርጩራ የኢኮ ቱሪዝም ሎጆች የተሠሩ ሥራዎች ለመንግሥት ቁርጠኝነት ማሳያዎች ናቸው።
የአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ በሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ የተሠሩ ማስፋፊዎችም የዘርፉን ከፍታ ለመጨመር ወሳኝ ሲሆን፣ አየር መንገዱ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ዓለም አቀፍ ተጓዦችን ቆይታ በማራዘም የኢኮኖሚውም የገጽታ ግንባታውም ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።
የተለወጠችው እና ለበርካታ ዓለም አቀፍ እና የአፍሪካ ስብሰባዎች ተመራጭ እየሆነች የመጣችው አዲስ አበባ ባለፈው ዓመት ብቻ ያስተናገደቻቸው ታላላቅ ኮንፈረንሶችም ለዘርፉ እያበበ መሔድ ትልቁን አስተዋፅኦ አድርጓል።
ባለፈው ዓመት ብቻ ከረሃብ ነፃ ዓለም ኮንፈረንስ፣ ለልማት የገንዘብ ድጋፍ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ፣ የአፍሪካ የሰላም ኮንፈረንስ፣ ስድስተኛው የአፍሪካ ብልጽግና ኮንፈረንስ፣ 46ኛው የካፍ መደበኛ ጉባኤ፣ የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ኮንፈረንስ፣ ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ጉበኤን ጨምሮ ከ150 በላይ ኮንፈረንሶች በአዲስ አበባ ተካሄደዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለፓርላማ ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት ላይ እንደጠቀሱት በእነዚህ ከ150 ሺህ በላይ ኮንፈረንሶች ለመሳተፍ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል።
በዓመቱ ከውጭ ቱሪስቶች በተጨማሪም 1.5 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች እንደ አንድነት ፓርክ፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ የወዳጅነት ፓርክ እና ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ያሉ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን በመጎብኘታቸው ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደተገኘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አክለዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከ13 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እነዚህ እነዚህን አካባቢዎች የጎበኙ ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥም ሆነ ዓለም አቀፍ ቱሪዝም ስበት ማዕከል መሆኑን ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በለሚ ታደሰ
#EBC #ebcdotstream #WorldTourismDay2025 #LandOfOrigins