ቱሪዝም በጉልህ የሚጠቀሰው በኢኮኖሚ ልማት ውስጥ ባለው ሚናው ቢሆንም፤ ለማኅበራዊ ዕድገት፣ ለትምህርት እና ለሥራ ዕድል ፈጠራም እርሾ በመሆን ያገለግላል።
የዓለም የቱሪዝም ቀን በየዓመቱ መስከረም 17 የሚከበር ሲሆን፤ ዘንድሮ “ቱሪዝም እና ዘላቂ ሽግግር” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር የተመድ መረጃ ያመላክታል።
ይህም አዎንታዊ ለውጥ በማምጣት ረገድ የቱሪዝምን አዳጊ እምቅ ዐቅም ለማመላከት እንደሆነ ተገልጿል።
የዓለም የቱሪዝም ባሮ ሜትር (World Tourism Barometer) መረጃ እንደሚያሳየው፥ የዓለም ቱሪዝም በፈረንጆቹ 2025 አጋማሽ የ5 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጥር እስከ ሰኔ በነበረው ጊዜ 690 ሚሊዮን ገደማ የቱሪስት ፍሰት የተመዘገበ ሲሆን፤ ይህም በ2024 ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የ33 ሚሊዮን ገደማ ብልጫ አለው።
የቱሪስት ፍሰት ከጨመረባቸው አካባቢዎች መካከል አፍሪካ አንዷ ስትሆን፤ አህጉሪቱ 12 በመቶ ዕድገት ካስመዘገበችው እስያ ፓሲፊክ ቀጥላ የ9 በመቶ ዕድገት አሳይታለች። የግጭት ቀጣና የሆነው መካከለኛው ምሥራቅ ያሳየው ዕድገት ደግሞ 1 በመቶ ብቻ ነው።
ኳታር የቱሪስት ፍሰቷን 158 በመቶ በማድረስ ከዓለም ቀዳሚዋ አገር ስትሆን፣ ሞሮኮ ደግሞ የ60 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ከአፍሪካ አንደኛ መሆን ችላለች።
በዘርፉ በርካታ ሥራዎችን እየሠራች ያለችው ኢትዮጵያ ደግሞ 52 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ከአፍሪካ ሁለተኛ እንደሆነች ነው መረጃው የሚያሳየው።
በቀጣይ ጊዜያትም አፍሪካ የተሻለች የቱሪስት መዳረሻ እንደምትሆን እና የ13 በመቶ ተጨማሪ ዕድገት እንደምታስመዘግብ ይጠበቃል።
የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንደሚሉት ቱሪዝም ኃይለኛ የለውጥ አንቀሳቃሽ ነው። የሥራ ዕድልን ይፈጥራል፤ የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚን ያነቃቃል፤ መሠረተ ልማቶችን ይደግፋል፤ እንዲሁም ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል።
ቱሪዝም በሰዎች፣ በባህል እና በወጎች መካል ያለውን ትሥሥር ያጠናክራል፤ በባህሎች መካከል ያለውን ድልድይ ይገነባል፤ ብዝኃነትን ያበለጽጋል።
በለሚ ታደሰ
#EBCdotstream #WorldTourismDay2025 #LandofOrigins