በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በጉባ ሰማይ ሥር በመላ ኢትዮጵያውያን አሻራ ተገንብቶ እውን የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የፈጠረው ንጋት ሐይቅ የተንጣለለ ውኃ ይዞ ይገኛል።
ሕዳሴ በኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ የተሰጠ የሰው ልጆችን ተስፋ የሚያለመልም፣ ለአካባቢው ልዩ ውበት እና ድምቀትን ያጎናፀፈ ነው።
ሐይቁ በርካቶች ሊጎበኙት የሚመኙት እና የሚያስቡት ድንቅ የእጅ ሥራ ነው ይላሉ የቱሪዝም ባለሙያው አቶ ናሆም አድማሱ።
አቶ ናሆም የታላቋ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማኅበር አባል እና የፕሌዠር ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅት ባለቤትም ናቸው።
በሕዳሴው ግድብ አማካኝነት የተፈጠረው ንጋት ሰው ሠራሽ ሐይቅ በዓለም ተወዳጅ የሆኑ የውኃ ላይ ስፖርቶችን እና ጨዋታዎችን ለማዘጋጀት እንደሚያስችል ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልጸዋል።
ሐይቁ 74 ቢሊዮን ኪዩብክ ሜትር ውኃ እንደሚይዝ፣ ከ70 በላይ ደሴቶች እንዳሉት፣ 187 ሺህ 400 ሔክታር ስፋት እንደሚሸፍን ይገለጻል።
ቱሪዝም መሠረተ ልማቶችን ማሟላትን ይፈልጋል የሚሉት ባለሙያው፣ በንጋት ሐይቅ ከአንደኛው ደሴት ወደ ሌላኛው ደሴት ለሚደረገው ጉዞ የሞተር ጀልባ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መጓጓዣዎች፣ ማረፊያዎች፣ ሆቴሎች እና የሰለጠነ የሰው ኃይል አስፈላጊ በመሆኑ፣ በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሃብቶች ዕድሉን ተጠቅመው ለበርካቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚያስችላቸው ጠቁመዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአካባቢውን የተፈጥሮ ሃብት አጠባበቅ፣ የግድቡን ኢንጂነሪንግ ሥራ፣ የቴክኖሎጂ እውቀት፣ ልምድ እና ተሞክሮ ለመቅሰም ከሀገር ውስጥ፣ እንዲሁም ከተለያዩ ሀገራት እንግዶች የሚመጡበት አግባብ ስለሚኖር፣ ቀድሞ መዘጋጀት አስፈላጊ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
እንግዶች በኢትዮጵያ ያላቸውን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም እንዲያስችልም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ቱሪስቶችን እንዴት መቀበል እንዳለባቸው፣ ሰፋ ያለ የንቃተ ኅሊና ሥልጠናዎችን በመስጠት የተፈጠረውን ዕድል በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊ ነው ይላሉ።
የታሪክ እና ፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር ዓለማየሁ አረዳ በበኩላቸው፥ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት ባሻገር ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያስተሳስር ትሩፋት ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ሥነሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ በንጋት ሐይቅ ላይ የተፈጠሩ ደሴቶች፣ የመዝናኛ ሪዞርቶችን በመገንባት፣ የትራንስፖርት አገልግሎቱን በማስፋት፣ የቱሪዝም አገልግሎቶችን በማሻሻል፣ የእንግዶችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም ለቤኒሻንጉል ጉመዝ ክልል ይዞት የመጣው ዕድል ሰፊ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።
በመሐመድ ፊጣሞ
#EBC #ebcdotstream #GERD #LakeNigat #tourism #worldtourismday