የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ በኒውዮርክ ከ80ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን በ3ኛው የብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል።
አምባሳደር ሃደራ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የብሪክስ አባል አገራት ዓለም አቀፍ ችግሮችን ለመፍታት የጋራ እርምጃቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ሰላምን በማፅናት፣ የባለብዙ ወገን ግንኙነትን በማጠናከር እና ዘላቂ የልማት ግቦችን በማሳካት በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚስተዋሉ ግጭቶች እና ሰብዓዊ ቀውሶች በልማት ላይ የሚያሳርፉትን ተፅዕኖ ለመቀነስ ብሪክስ ታሪካዊ ዕድል እንዳለው ገልጸዋል።
በሪዮ ጉባዔ የጸደቀው በአየር ንብረት ፋይናንስ፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት አስተዳደር እና በሽታዎችን በመከላከል የተደረሰው ውሳኔ ለብሪክስ ሁነኛ መመሪያ ሆኖ የሚያገለግል ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላምና ልማት የጋራ ጥረት ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗንም አምባሳደር ሃደራ አረጋግጠዋል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን የጋራ የመገናኛ ብዙኃን መግለጫን በማጽደቅ ተጠናቋል።
#ebcdotstrem #brics #ethiopia #mfa