Search

ለናይጄሪያውያን መማማሪያ ሆኖ የቀረበው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ

እሑድ መስከረም 18, 2018 1848

ማኅበራዊ ሃያሲ፣ የሰላም እና የማኅበራዊ ፍትህ ተሟጋች የሆነው ጃቢር ኡስማን "ኦፒኒየን ናይጄሪያ" በተባለው ሚዲያ ላይ ስለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚያትት ጽሑፍ አቅርቧል።

በጽሑፉ ናይጄሪያ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ልትማር የሚገባቸውን ጉዳዮችንም አንሥቷል።

ኡስማን ጽሑፉን የሚጀመረው "ጥሩ ጅማሬ የፍጻሜው ግማሽ መንገድ ነው" በሚለው የግሪኩ ፈላስፋ አሪስቶትል ሐሳብ ነው፡፡

ይህ ጊዜ የማይሽረው ሐሳብ የሚያጋጥሙ መሰናክሎች ምንም ያክል ከባድ ቢሆኑ፣ የማንኛውም ታላቅ ስኬት መሠረት አንድን ሥራ ለመጀመር ያለን ድፍረት መሆኑን ያስታውሰናል ይላል ጸሐፊው።

የሕዳሴ ግድብም ለዚህ ሐሳብ ሕያው ምስክር ነው በማለት ይቀጥላል።

ብዙ ጊዜ ናይጄሪያ ውስጥ የሚጀመሩ ብሔራዊ ጥቅም ያላቸው ታላላቅ ፕሮጀክቶች በጥቃቅን የሀገር ውስጥ ተቃውሞ ወይም የውጭ ጫና እንደሚቋረጡ ጠቅሶ፣ ኢትዮጵያ ሕዳሴን ለመገንባት ያሳየችው ቆራጥነት ለናይጄሪያ ጠቃሚ ትምህርት እንደሚሆን ያወሳል።

አንድ ጠቃሚ ፕሮጀክት ከተጀመረ ምንም ዓይነት መሰናክል ቢያጋጥም ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አስፈላጊ መሆኑንም የኢትዮጵያ ቁርጠኝነት ምሳሌ መሆኑን ያሳያል።

የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በአፍሪካ የእዕድገት ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዳለውም ያስረዳል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ሕዳሴን እውን ለማድረግ ላደረገው የተቀናጀ ጥረት ከፍተኛ አድናቆት እንደሚገባውም ገልጿል።

ሕዳሴ ግድብ በደካማ አፈጻጸም፣ በሙስና እና በጥራት መጓደል ከሚቋረጡት በርካታ የአፍሪካ ፕሮጀክቶች በተለየ መልኩ ቆራጥነት፣ የሀገር ፍቅር እና የዓላማ አንድነት ምን ሊያሳካ እንደሚችል ትምህርት እንደሰጠ ያትታል ጸሐፊው።

የፕሮጀክቱ ልዩ እና አበረታች ከሆኑት ገጽታዎች አንዱ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ያበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሆነም ይጠቅሳል።

ኢትዮጵያውያን ይህንን ግዙፍ ግድብ እውን ለማድረግ ከደመወዛቸው እና ከገቢያቸው አካፍለው በፈቃደኝነት አስተዋፅኦ አድርገዋል ይላል ኡስማን።

እንደዚህ ዓይነት የመሥዋዕትነት መንፈስ እና በጋራ መቆም በዛሬው አፍሪካ ብርቅ ነው የሚለው ኡስማን፣ ዜጎች ፕሮጀክቶች ሕይወታቸውን በቀጥታ እንደሚያሻሽሉ ሲያምኑ ጊዜያዊ ምቾታቸውን ለዘለቄታው ዕድገት መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን ኢትዮጵያውያን ማሳያ መሆናቸውን ያነሣል።

ግድቡ የተጠናቀቀው ተግዳሮቶች ሳይገጥሙት እንዳልሆነ የሚጠቅሰው ጸሐፊው፣ ከግብፅ እና ከሱዳን የገጠሙት ፈተናዎች በጣም ከባዶቹ እንደነበሩ አውስቷል፡፡

ነገር ግን ግድቡ ለራሷ ልማት አስፈላጊ መሆኑን የምታምነው ኢትዮጵያ በአንጻሩ ማንም ላይ ጉልህ ተፅዕኖ እንደማያመጣ ግልጽ አድርጋ የገጠሟትን ተግዳሮቶች በፅናት በመወጣት ሕዳሴን ማጠናቀቋን ይገልጻል፡፡

የኢትዮጵያ ቆራጥነት ለናይጄሪያ ጠቃሚ ትምህርት እንደሚሆን ጠቅሶ፣ ሕዳሴ ምንም ዓይነት መሰናክሎች ቢያጋጥሙ እንኳን የጀመሩትን ከማቋረጥ በዓላማ ፀንቶ የጀመሩትን በትኩረት ማጠናቀቅ እንሚያስፈልግ ያሳያል ብሏል።

ሕዳሴ የኢትዮጵያን የኃይል አቅርቦት በእጅጉ እንደሚያሳድገው፣ ይህም ኢትዮጵያን ከኃይል አቅርቦት እጥረት በማሳረፍ የኢኮኖሚ ዕድገቷን እንደሚያሳልጥ ገልጿል፡፡

ይህ ውጤት የተገኘው በኢትዮጵያ መንግሥት የአመራር ቁርጠኝነት እንደሆነ ጠቅሶ፣ ተመሳሳይ አቅም ያላት ናይጄሪያም ከነዳጅ ጥገኝነት የሚያላቅቃትን ሥራ ለመሥራት ከዚህ መማር እንዳለባት ምክረ ሐሳብ አቅርቧል።

ኢትዮጵያውያን ከጥሪታቸው አካፍለው ይህን ግዙፍ ግድብ መሥራት ከቻሉ ናይጄሪያውያንም የሚያስተባብራቸው ካገኙ ይህን ማድረግ እንደሚችሉ ገልጾ፤ ሕይወትን የሚለውጥ ልማት እንዲሁ በቀላሉ ሳይሆን በመሥዋዕትነት የሚመጣ መሆኑን ያሰምርበታል፡፡

 

በለሚ ታደሰ

#EBC  #ebcdotstream  #GERD