ጠቅላይ ሚኒስርትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ-ግብር በሀላባ እና ካምባታ ዞኖች የተገነቡ ሞዴል መንደሮችን አስረክበዋል።
መንደሮቹ መንግሥት የአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮችን ሕይወት ለማሻሻል የሚያደርገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ማሳያ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
ቤቶቹ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ የተገጠመላቸው፣ ለማብሰል ደግሞ ከእንስሳት እዳሪ ባዮጋዝ የሚጠቀሙ፣ የተለየ ሳሎን፣ መጸዳጃ እና ሰርቪስ ቤቶች የተሟላላቸው መሆናቸውንም በማኅበራዊ ሚዲያ ትሥሥር ገጻቸው ገልጸዋል።
"ንጽህናን በሚያረጋግጥ እና የአኗኗር ደረጃን ከፍ በሚያደርግ አኳኋን የተለየ የእንስሳት በረት ተሰርቶላቸዋል" ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
እነዚህ የገጠር ኮሪደር ልማት መንደሮች የመንግሥት የገጠሩን አኗኗር የማሳደግ ሕልም አካል በመሆን ተስፋፍተው የሚሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
"ባለፉት ሰባት አመታት የክረምት በጎ ፈቃድ በከተሞች ለሚኖሩ ለችግር የተጋለጡ ወገኖች መኖሪያ ቤቶችን ስናቀርብ ቆይተናል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁን ደግሞ በገጠር ኮሪደር ልማት የሥራው እመርታ ወደገጠር መስፋፋቱን አስታውቀዋል።
ግለሰቦች፣ ድርጅቶች እና የዲያስፖራው ማኅበረሰብ እነኚህን ሥራዎች እንዲደግፉ እና እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ቀድሞ በነበረው ጉብኝታቸው ወቅት ያቀረቡላቸውን የቤት ሥራ በመወጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ በራስ አቅም የሀምበሪቾ ተራራ ደረጃንም በእጥፍ ሠርተው ላጠናቀቁት አመራሮች ምስጋና አቅርበዋል።
ወደፊትም የየአካባቢ አመራሮች ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሠሩትን ሞዴል መንደሮች በመጪው አመት በየዞኑ ወደ 100 ቤቶች እንዲያሳድጉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አሳስበዋል።