Search

ሀገራዊ ኢኒሼቲቮችን ከመደበኛ ሥራዎች ጋር በማጣጣም ለማሳካት በትኩረት ይሠራል - አህመዲን ሙሐመድ (ዶ/ር)

ቅዳሜ ሰኔ 20, 2018 51

በአማራ ክልል የከተማ ልማት ክላስተር የክረምት ወራት የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች የትግበራ ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሂዷል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አህመዲን ሙሐመድ (/) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ በቀጣይ የክረምት ወራት በክላስተሩ በታቀፉ ተቋማት  የሚፈጸሙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ታቅደው ወደ ሥራ ተገብቷል።

/ አህመዲን፣ በዕቅዱ ከመደበኛ ሥራዎች ጎን ለጎን ለሀገራዊ ኢኒሸቲቮች ትግበራ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸው፤ ለአብነትም የከተሞች ኮሪደር ልማትን የማስፋት ሥራ በክረምቱ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል መሆኑን አንስተዋል።

በተቋማት የተገልጋይ እርካታን እያረጋገጠ የሚገኘው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልሉ 4 ከተሞች እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ አገልግሎቱን ወደ ሌሎች ከተሞች ለማስፋትና በግንባታ ላይ የሚገኙ ማዕከላትን በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ለማስገባት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

በክልሉ 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተው፣ በቀጣይም ቀሪ ዜጎች እንዲመዘገቡ የንቅናቄ ሥራ ለማከናወን መታቀዱን ጠቁመዋል።

በኮደርስ ስልጠና እና የኑሮ ውድነትን በመቀነስ ረገድ የተቀመጡ ግቦችን እንዲሁም ሌሎች ሀገራዊ ኢኒሼቲቮችን ከመደበኛ ሥራዎች ጋር በማጣጣም ለማሳካት በትኩረት ለመሥራት በዕቅድ መያዙንም ተናግረዋል።

በሳሙኤል ወርቃየሁ