Search

የፍቅር እና የረጅም ዕድሜ ተዓምር፦ በጥምረት 316 ዓመታት የኖሩትና ሳይንቲስቶችን ያስገረሙት የብራዚል እህትማማቾች አስገራሚ ታሪክ

እሑድ ሰኔ 21, 2018 66

በመካከላቸው ባለው ጠንካራ የቤተሰብ ትስስርና በማይበጠስ ፍቅራቸው የዓለምን ትኩረት የሳቡ ሦስት የብራዚል እህትማማቾች፣ በጥምር 316 ዓመታት 302 ቀናት ዕድሜ በማስመዝገብ አዲስ የዓለም ድንቅ ክብረ ወሰን (ሪከርድ) ይዘዋል።

ይህ አስገራሚ ክስተት በሰዎች ረጅም ዕድሜ ላይ የሚመራመረውንሎንግቪኩዌስት” (Longeviquest) የተሰኘውን ተቋም ጨምሮ በርካታ ሳይንቲስቶች የዕድሜያቸውን ምስጢር ለማወቅ ምርምር እንዲጀምሩ አነሳስቷቸዋል።

ከእህትማማቾቹ መካከል ትልቋ እህት ሌቪታ 109 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ስትሆን፣ ወላጆቿ በእርሻ ሥራ ላይ በነበሩበት ጊዜ ታናናሾቿን የመንከባከብ ኃላፊነት ስላለባት ትዳር ሳትመሠርትና ልጅ ሳትወልድ ሙሉ ሕይወቷን ለቤተሰቧ የሰጠች ሲሆን በትርፍ ጊዜዋም ስፌትና ሹራብ ትሠራለች።

መካከለኛዋ ዞራይድ በበኩሏ 104 ዓመት ዕድሜ ያላት ሲሆን፣ በመጀመሪያ መምህርት የነበረች ቢሆንም በኋላ ግን ወደ ነርሲንግ ሙያ በመግባት እስከ ጡረታዋ ድረስ በሆስፒታሎች ሕዝብን አገልግላለች፤ እሷ ትዳር መሥርታ 5 ልጆችንም አፍርታለች።

ታናሿ እህት ዙሊና ደግሞ 103 ዓመት ዕድሜ ያላት ሲሆን፣ ትዳር መሥርታ ባለቤቷ በባቡር ሐዲድ ዘርፍ ሲሠራ እሷ ደግሞ 6 ልጆቻቸውን በፍቅር በማሳደግና ቤተሰቧን በመምራት ሕይወቷን አሳልፋለች።

እነዚህ እህትማማቾች ባለፉት አሥርት ዓመታት ሁሉ ሳይነጣጠሉ በአንድነት የኖሩ ሲሆን፣ በሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ሁሉ እርስ በርስ በመደጋገፍና በመተጋገዝ ቆይተዋል።

ዛሬ ለደረሱበት አስደናቂ የዓለም ክብረ ወሰን ትልቁ ምስጢራቸውየማይበጠስ የቤተሰብ ፍቅርና አንድነትመሆኑን መግለጻቸው ብዙዎችን አስገርሟል። የምርም ፍቅር ዕድሜን ያረዝማል ማለት ይህ ነው።

በብሌን ደንበሎ