Search

ለአፍሪካ ሃገራት የተቀናጀ የመድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያዎች አቅርቦትን ለማመቻቸት ያለመው ምክክር

ማክሰኞ ጥቅምት 04, 2018 40

የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ከአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ጋር በመተባበር በአፍሪካ የተቀናጀ የመድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያዎች ግዢ እና አቅርቦት ሜካኒዝም ጅምር ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡
ውይይቱ የአፍሪካ ሲዲሲ በጋራ በሚሰበሰብ ፈንድ የመድኃኒት ምርቶችን እና ክትባቶችን በመግዛት ለአባል ሀገራት ማሰራጨት እና የሃገር ውስጥ ምርትን ለማበረታታት የሚያስችለው መሆኑ ተመላክቷል።
በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የአፍሪካ ዋነኛ የጤና ስርዓት ተግዳሮቶች አንዱ የመድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያዎች ግዢ እና አቅርቦት መሆኑን ጠቁመዋል።
አፍሪካ ሲዲሲ ይህንን አሳሳቢ ችግር ለመፍታት ላደረገው አመራርም አመስግነዋል።
 
 
ስብሰባው ከተለያዩ ሀገራት የተቀናጀ የመድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያዎች ግዢ እና አቅርቦት ልምድ ለመቅሰም እና ቀጣናዊ ትብብርን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ እንዲሁም ሀገራዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ለመለየት የሚረዳ ጠቃሚ መድረክ ነው ብለዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬሕይወት አበበ ኢትዮጵያ ለሀገር ውስጥ ፋርማሲዩቲካል ምርቶች ቅድሚያ እንደምትሰጥ ገልጸው፤ በአህጉራዊ ትብብር የአፍሪካ ሀገራት በጋራ ተጠቃሚ መሆን እና ዘላቂ የጤና ስርዓቶችን መገንባት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ውይይቱ በአህጉሪቱ አጠቃላይ የሕዝብ ጤና እና የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪን ለማሳደግ ወደ ሚረዳ ወደ አንድ፣ ግልፅ እና ቀልጣፋ የግዥ ሂደት ለማምጣት ክልላዊ ጥረቶችን በማጣጣም ረገድ ትልቅ ምዕራፍን አሳይቷል።
ኢትዮጵያ የተቀናጀ የመድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያዎች ግዢ እና አቅርቦት ትግበራ ለመጀመር የመግባቢያ ሰነድ ከፈረሙ 10 ሃገራት አንዷ ናት፡፡