Search

በቀጣናው የሚገኙ አፋሮችን ለዘመናት ያስተሳሰረው ባህላዊ ሥርዓት

ማክሰኞ የካቲት 03, 2018 37

በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የሚኖሩ አፋሮች ለዘመናት አንድነታቸውን እንዲያጎለብቱ ያስቻሉ ባህላዊ ሥርዓቶችን በማጠናከር ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።
የአፋር ሕዝብ ቋንቋ፣ ባህል እና ሁለንተናዊ መገለጫ የሆነው ''አፋሬ'' ጉባኤ በሠመራ ከተማ ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአፋር ሕዝብ ሁለንተናዊ መገለጫ የሆነው “አፋሬ መድዓ” በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ አፋሮችን ያስተሳሰረና ለዘመናት የቆየ ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓት መሆኑን አስታውቀዋል።
የአፋሬ መድዓ ዋነኛ ግብ አጥፊን መቅጣት ብቻ ሳይሆን፣ ተበዳይ ካሳ እንዲያገኝ ማድረግ እና ዘላቂ እርቅ ማውረድ በመሆኑ የፍትሕ ሥርዓቱን ለትውልድ ማሻገር እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ያሏትን ባህሎች በሚገባ በማስተዋወቅ የቱሪዝም መስህብ እንዲሆኑ ለማስቻል በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አንስተዋል።
የአፋር ሕዝብ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት "አፋሬ መድዓ"ን (Qafarre Madqa) ዓለም አቀፍ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ የተጀመሩ ሥራዎችን መኖራቸውን ጠቁመዋል።
የጂቡቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ነጊብ አብደላ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ለዘመናት ጸንቶ በቆየ ባህል፣ ቋንቋና ኃይማኖት የተሳሰሩ ወንድማማች ሕዝቦች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የ"ሄር-ኢሴ" ባህላዊ ዳኝነት በዩኔስኮ መመዝገቡን ያስታወሱት ነጊብ አብደላ፤ የሁለቱን ወንድማማች ሕዝቦች እና ሀገራት ሁለንተናዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ እንደሚሄድም አመላክተዋል።
ጉባኤው እስከ የካቲት 5 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ሲሆን፤ በዛሬው የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ የአፋር ሱልጣኖች፣ የጎሳ መሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች፣ እንዲሁም የጅቡቲ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
 
በሁሴን መሀመድ