Search

የኢትዮጵያዊው ዐሻራ ያረፈበት የአፍሪካ ኅብረት ሰንደቅ ዓላማ

ሓሙስ የካቲት 05, 2018 92

በአፍሪካ ኅብረት አደባባዮች እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ከፍ ብሎ የሚውለበለበው አረንጓዴው ሰንደቅ ዓላማ የአንድ ብርቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የጥበብ ውጤት መሆኑን የሚያውቁት ጥቂቶች ናቸው። 

ይህ ባለታሪክ በመርካቶ አድጎ የጥበብ ዓለምን የተቀላቀለው ሠዓሊ እና የግራፊክስ ባለሙያ፣ በዜግነት አሜሪካዊ የሆነው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ያዴሳ ዘውገ ቦጂአ ነው። 

የአፍሪካ ኅብረት በ2000 ዓ.ም (እ.ኢ.አ) አዲስ መለያ እንዲኖረው ባቀረበው ጥሪ መሠረት፣ ያዴሳ ከ19 ሀገራት የተውጣጡ ከ100 በላይ ተወዳዳሪዎችን በማሸነፍ አህጉሪቱን የሚወክል ድንቅ የፈጠራ ሥራ ለዓለም አበርክቷል።

ይህ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2002 ዓ.ም በይፋ የጸደቀው ሰንደቅ ዓላማ፤ የአፍሪካን ካርታ በአረንጓዴ ቀለም መወከሉ አህጉራዊ ተስፋን እና መልካም ምኞትን የሚያሳይ ሲሆን፣ ዙሪያውን የከበቡት 55 ወርቃማ ኮከቦች ደግሞ የአባል ሀገራቱን አንድነት እና ብልፅግና ይወክላሉ። 

ከካርታው በስተጀርባ ያሉት ነጭ የፀሐይ ጨረሮች አፍሪካውያን ከቀሪው ዓለም ጋር በሰላም እና በወዳጅነት የመኖር ፍላጎታቸውን የሚያንፀባርቁ ናቸው። 

ያዴሳ በቀድሞው ሰንደቅ ዓላማ ላይ የነበረውን እና የትግል ምልክት ተደርጎ የሚወሰደውን ቀይ ቀለም በመተው፣ አህጉሪቱ ከቁስሏ ድና ወደ ብሩህ የወደፊት ጊዜ የምታደርገውን ጉዞ በፈጠራው ለመግለጽ ችሏል።

ያዴሳ አሸናፊ መሆኑን ያወቀበት አጋጣሚም እጅግ አስገራሚ ነበር፤ በአንድ ምሽት የሲኤንኤን ቴሌቪዥን ሲመለከት ጋዜጠኛ ላሪ ኪንግ ከሊቢያው መሪ ሙዓመር ጋዳፊ ጋር በሚያደርጉት ቃለ ምልልስ ጀርባ፣ የራሱ ዲዛይን በክብር ተሰቅሎ በማየቱ በደስታ ጮኸ።

በመርካቶ ግርግር እና ብርቱ ሕይወት ውስጥ ያደገው ይህ ጠቢብ፣ የዲዛይን ውበትን ብቻ ሳይሆን አፍሪካውያን የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው እንዲወስኑ የሚያሳስብ የራዕይ ሰነድ ጭምር በማቅረቡ የአህጉሪቱን መሪዎች ልብ መግዛት ችሏል።

ዛሬ ያዴሳ ቦጂአ በሳላቸው ቀለማት እና ቅርፆች አማካኝነት የኢትዮጵያ የጥበብ አሻራ በመላው አህጉር ኩራት ሆኖ ለዘለዓለም ተመዝግቧል። 

የአፍሪካ ኅብረት መዝሙርም በተመሳሳይ መልኩ በታላቁ ኢትዮጵያዊ ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን የተደረሰ መሆኑ ይታወቃል። 

በያዴሳ ቦጂአ የፈጠራ አሻራ የደመቀው ሰንደቅ ዓላማም ሆነ በሎሬት ፀጋዬ ስንኞች የከበረው የአህጉሪቱ መዝሙር፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያላትን ጥልቅ ፍቅር እና የማይከስም አበርክቶ የሚያሳዩ ኅያው ምስክሮች ናቸው። 

ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን እና ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነፃነት ቀንዲል ሆና የቆየችው በቃል ብቻ ሳይሆን፣ በተግባር በከፈለችው መሥዋዕትነት ጭምር ነው።

ከጥንታዊው የዓድዋ ድል ጀምሮ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መናኸሪያ በመሆን፣ አህጉራዊ ተቋማትን ከመገንባት ባለፈ የአፍሪካውያንን ድምፅ ለዓለም በማሰማት ረገድ ኢትዮጵያ ቀዳሚውን ስፍራ ትይዛለች። 

አህጉሪቱ የራሷ ዓርማ፣ የራሷ መዝሙር እና የራሷ መገለጫ እንዲኖራት ኢትዮጵያ ያበረከተችው ድርሻ፣ ሀገራችን ለጥቁር ሕዝቦች ኩራት እና ለነፃነት ትግላቸው ዋቢ መሆኗን ዳግም ያረጋገጠ ነው። 

ዛሬም እንደ ትናንቱ ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን የጋራ ቤት፣ የጥበብ ምንጭ እና የሉዓላዊነት ተምሳሌት ሆና ትቀጥላለች። 

 

በላሉ ኢታላ