Search

የሚዲያ ልህቀት ማዕከሉ ባለሙያዎችን በማብቃት ረገድ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

ሓሙስ ጥቅምት 06, 2018 109

የኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል ይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር ተካሂዷል።
በወቅቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ በኢትዮጵያ መልክ የተቋቋመው የሚዲያ ልህቀት ማዕከል የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ የመረጃ ተደራሽነትን ለማስፋት የጎላ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ማዕከሉ የዘርፉን ባለሙያዎች በማሰልጠን እና ብቁ እንዲሆኑ በማስቻል ወሳኝ ድርሻ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።
ሚዲያዎች የልህቀት ማዕከሉን በመጠቀም ሥራዎቻቸውን ማሳደግ እንዳለባቸውም አመላክተዋል።
 
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን በአራት ጉዳዮች ላይ ወጥ አረዳድ እና የይዘት ስምምነት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።
በተለይም ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር፣ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር፣ የወል ትርክትን መገንባት እና የብልፅግና እሳቤን ማስረፅ መገናኛ ብዙሃን ሊሰሩባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውን አብራርተዋል።
አራቱን ጉዳዮች ከሙያዊ መርኅ ጋር በማጣጣም መተግበር ይገባል ያሉት ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል፤ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ወጥ የሆነ አረዳድ ሊኖቸው እንደሚገባም ገልፀዋል።
በመርሀ-ግብሩ ላይ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል የተቋቋመው በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አማካኝነት መሆኑ ተመላክቷል።
በቤተልሔም ገረመው እና በኤልሻዳይ ወንድማገኝ