የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር “ዘላቂ የደን ልማት አያያዝና አጠቃቀም” በሚል ዘርፍ ከዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) እውቅና አግኝቷል።
የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው የአረንጎዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ተጨባጭ ውጤት በማስመዝገቡ እና እውቅና በማግኘቱ ደስታቸውን ገልጸዋል።
ከ47 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል አረንጎዴ ዐሻራን በቁርጠኝነት ተግባራዊ እያደረገች የምትገኘው ኢትዮጵያ፤ ላስመዘገበችው ስኬት በዓለም መድረክ ዕውቅና ማግኘቷ የሚገባት መሆኑንም ነው ያስረዱት።
ኢትዮጵያ በአረንጎዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ትግበራ የመጀመሪያዎቹ አራት ዓመታት የደን ሽፋኗ ከነበረበት ከ17.2 በመቶ ወደ 23.6 በመቶ ማሳደግ መቻሉንም የቱሪዝም ሚኒስትሯ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያዊያን በአንድነት የነገ ተስፋ የሆኑትን ችግኞች በመትከል እንዴት ታሪክ መሥራት እንደቻሉ እና ተስፋ ወደ ተግባር ሲለወጥ ምን አይነት ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል ወደኢትዮጵያ መጥታችሁ በመመልከት መመስከር ትችላላችሁ ሲሉም ሚኒስትሯ በጣሊያን ሮም በተካሄደው የዓለም የምግብ ጉባዔ ላይ ተናግረዋል።
በመሀመድ ፊጣሞ