Search

የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

ሓሙስ ጥቅምት 06, 2018 67

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበራት ፌዴሬሽን ከክርስቲያን ብላይንድ ሚሽን ጋር በመተባበር "ኢትዮጵያን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እናድርግ" በሚል መሪ ሃሳብ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ጉባዔ አካሂዷል፡፡
የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓባይነህ ጉጆ፤ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
 
በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች እንደሚገኙ ጠቁመው፤ መንግሥት የአካል ጉዳተኞችን ችግሮች ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎችን እየሰራ ቢሆንም አሁንም ብዙ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ችግር ለመፍታት በዝግጅት ላይ ያለውን ፖሊሲ አጠናቅቆ ወደ ሥራ ማስገባት፣ የፋይናንስ ድጋፍን እና የማኅበረሰብ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶችን ቁጥር ማሳደግ እንደሚገባም ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በበኩላቸው፤ የአካል ጉዳተኞችን አካታችነት ማረጋገጥ ከተቻለ እርዳታ ተቀባይ ሳይሆኑ ንቁ የለውጥ ሃይል መሆን ይችላሉ ብለዋል።
ጉባዔው የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ከክርስቲያን ብላይንድ ሚሽን (CBM)፣ ከሴቶችና የማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከጤና ሚንስቴር ጋር በጋራ የተዘጋጀ ነው፡፡
 
በላሉ ኢታላ