የኢትዮጵያ ነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ደስታው መኳንንት (ዶ/ር) በኢቢሲ ዳጉ ፕሮግራም ላይ ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ ብዙ ሐገራት ከድህነት የወጡት የተፈጥሮ ሐብታቸውን ተጠቅመው መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያም የከርሰ-ምድር ሐብቷን መጠቀም መጀመሯ ለእድገቷ መነሻ እንደሚሆናት ጠቁመዋል፡፡
የስራ እድል ለመፍጠር እና ከድህነት ለመውጣት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚጠይቁ ስራዎች መከናወን እንደሚገባቸው ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ይህንን ችግር ለማስወገድ አንደኛው መንገድ መሆኑን ነው የገለፁት፡፡
የመጀመሪያ ምዕራፍ የኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ መመረቅ እና እየተሰራ ያለው ሁለተኛው ምዕራፍ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ኢኮኖሚው እያደገ ሲሄድ የሚፈልገውን የኃይል አቅርቦት ለመሸፈን እንደሚያግዝ ገልፀዋል፡፡
በ2017 ወደ ሐገር ውስጥ ከገባው 4.3 ቢሊዮን ሊትር ነዳጅ አብዛኛው ለተሽከርካሪዎች የዋለ ቢሆንም 8 በመቶ ለኢንዱስትሪ አገልግሎት እንደሚውል የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ይህን የኃይል ፍላጎት በመሸፈን ረገድ እገዛ እንደሚያደርግ አንስተዋል፡፡
አሁን የወጣው የተፈጥሮ ጋዝ እና በመሰራት ላይ የሚገኘው የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ለኢኮኖሚው ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል፡፡
በንፍታሌም እንግዳወርቅ
#EBC #EBCDOTSTREAM #Ethiopia #naturalgas