ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ እና ከአውስትራሊያ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ታስገባ የነበረውን የድንጋይ ከሰል ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚያስችል ግዙፍ ፋብሪካ ተገንብቶ ሥራ ጀመረ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የተገነባውን እና በዓይነቱ ልዩ የሆነውን የአርጆ የድንጋይ ከሰል ማቀነባበሪያ ፋብሪካን መርቀው ከፍተውታል።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አሕመድ እንደገለጹት ፋብሪካው በሰዓት 200 ቶን የማምረት አቅም ያለው ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ካሉ መሰል ፋብሪካዎች በትልቅነቱ ቀዳሚ ነው።
ምርቱም ከውጭ ከሚገቡት በተሻለ እስከ 6 ሺህ 600 ‘ካሎሪ ቫልዩ’ ጥራት ያለው የድንጋይ ከሰል የሚያመርት በመሆኑ ለኢንዱስትሪዎች ብቁ ግብዓት መሆን ይችላል።
ይህ ፋብሪካ ምንም ዓይነት የውጭ ኬሚካል ሳይጠቀም የሀገሪቱን ተፈጥሮአዊ ሀብት ብቻ በማቀነባበር ለገበያ የሚያቀርብ በመሆኑ፣ ለኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱ ተገልጿል።
በተለይም ለትላልቅ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ተደራሽ በመሆን ለውጭ ምንዛሬ የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ በማዳን ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታል።
በቢታንያ ሲሳይ