በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በ'ገበታ ለትውልድ' መርሐ ግብር የተገነባውና የኢትዮጵያን የተደበቀ ውበት ለዓለም ያሳየው ሸበሌ ሪዞርት በድንቅ ሁኔታ ተጠናቆ ለምረቃ በቅቷል።
ይህ ሪዞርት ከሶማሊ ክልል ርዕሰ መዲና ጅግጅጋ በ28 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ 380 ሄክታር በሚሸፍን የተፈጥሮ ስጦታ ላይ ያረፈ ድንቅ ስፍራ ነው።
ሸበሌ ሪዞርትን ምን ልዩ ያደርገዋል? ሪዞርቱ ከአካባቢው ምልክትና ባህል ጋር በተቆራኘ መልኩ "የተኙ ግመሎችን" ቅርፅ ይዞ መገንባቱ ለየት ያለ የሥነ-ሕንጻ ጥበብ የተላበሰ ያደርገዋል።

ይህ የፈጠራ ውጤት ከሩቅ ለሚያየው ሰው ሕንፃ ሳይሆን የተፈጥሮ አካል ይመስላል። በተጨማሪም በታሪካዊው የሸበሌ ወንዝ ዳርቻ ላይ መቆርቆሩ ንፁሕ አየር ለመተንፈስና የውኃውን ዜማ እየሰሙ መንፈስን ለማደስ ወደር የሌለው ምርጫ ያደርገዋል።
የባህላዊ እና ዘመናዊ ጥበብ ቅኝት የሶማሌን ድንቅ ባህላዊ አርክቴክቸር ከዓለም አቀፍ የቱሪዝም ደረጃ ጋር ያጣመረው ሸበሌ ሪዞርት፤ ስምንት ውብ መንደሮችን እና 13.5 ኪሎ ሜትር ዘመናዊ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን አካቷል።
ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ይህ ፕሮጀክት የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ወደ አዲስ ከፍታ የሚያሸጋግር ከመሆኑም በላይ፣ ለአካባቢው ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር የቀጣናው የኢኮኖሚ ሞተር ሆኖ ያገለግላል።

ሥራው ለዕይታ ብቻ ሳይሆን ለትውልድ የሚሻገር አሻራ በመሆኑ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ሪፎርም በውጤታማነት ከሚያሳኩ ተግባራት መካከል አንዱ ነው።
ከከተማ ጫጫታ ርቀው፣ በሸበሌ ወንዝ ዳርቻ ውብ የሆነውን የፀሐይ ግባት (Sunset) ለመመልከት እና የኢትዮጵያን ብዝኃ-ውበት ለማድነቅ ሸበሌ ሪዞርት ቀዳሚ ምርጫዎ እንደሚሆን አንጠራጠርም።
በለሚ ታደሰ