በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የገበታ ለትውልድ መርሐ-ግብር የተገነባው የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ዛሬ በይፋ ተመርቋል።
ሪዞርቱ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን የሄሊኮፕተር ማረፊያን አካትቶ ነው የተገነባው።
ይህ መሠረተ ልማት ሪዞርቱ ለሀገር ውስጥ እና ለዓለም አቀፍ ቱሪስቶች በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆን የሚያስችለው ሲሆን፣ የቱሪዝም መዳረሻውን ለመጎብኘት ለሚመጡ እንግዶች ምቹና ፈጣን የጉዞ አማራጭ ይፈጥራል።
በ13 ነጥብ 3 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ሪዞርት፣ ከሄሊኮፕተር ማረፊያው በተጨማሪ ዘመናዊ የመዝናኛ አማራጮችን ይዟል።

3 ነጥብ 70 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ጥራት ያለው የአስፋልት መንገድ የተዘረጋለት ሪዞርቱ፣ በተለያዩ የፍራፍሬ ዞኖችና ለዓይን በሚማርኩ አረንጓዴ ስፍራዎች የተከበበም ነው።
እንዲህ ያለው ዘመናዊ ግንባታ የአካባቢውን አስደማሚ ታሪክ ለዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
ሪዞርቱ የወሎን ሕዝብ ባህላዊ እሴትና እንግዳ ተቀባይነት ለዓለም የሚያስተዋውቅ ታላቅ ገበታ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፣ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገጽታ ወደ አዲስ ከፍታ ያሸጋገረና ለትውልድ የሚተላለፍ ድንቅ ዐሻራ ነው።
በለሚ ታደሰ