በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እያንሰራራ ያለውን የኢንዱስትሪ እና የኢንቨስትመንት ዘርፍ ይበልጥ ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።
አቶ መላኩ በአማራ ክልል ኮምቦልቻ ከተማ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ሚኒስትሩ ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት ማብራሪያ፥ ኢንቨስትመንት እና አምራች ኢንዱስትሪን የሀገሪቱ የብልጽግና ማዕከል ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ምርታማነትን ማሳደግ እና አዳዲስ ባለሃብቶችን መሳብ መቻሉን አንስተዋል።
በዚህም ተኪ እና የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ምርቶችን በጥራት፣ በዓይነት እና በብዛት በማምረት፤ እንዲሁም ዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
ባለፈው የበጀት ዓመት ከ4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተኪ ምርት መመረቱን ጠቅሰው፤ ዘንድሮም ከ5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተኪ ምርት ለማምረት እየተሠራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ እንድሪስ አብዱ፥ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል፣ የብድር እና የቦታ አቅርቦቶችን በማፋጠን ዘርፉ እንዲነቃቃ ማስቻሉን ገልጸዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መሀመድ አሚን የሱፍ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅንቄ ዘርፉን ከማነቃቃቱ ባለፈ ተኪ ምርት እንዲጨምር ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ሲሉ ተናግረዋል።
#ebcdotstream #ethiopia #industry #manufacturing #investment