የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ከዓለም ባንክ እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ስብሰባዎች ጎን ለጎን ከእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አጃይ ቡሻን ፓንዲ ጋር ተወያይተዋል።
አቶ አሕመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት በተለይ አዳጊ ሀገራት ቅድሚያ ለሚሰጧቸው የልማት ፕሮጀክቶች በአነስተኛ ወለድ በረጅም ጊዜ የሚመለስ ብድር አገልግሎትን ማስፋት በጣም አስፈላጊ ስለመሆኑ አንስተዋል።
ባንኩ ባለፉት አስር ዓመታት በጣም ወሳኝ የሆኑ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ በማድረግ ረገድ ላሳየው ተነሳሽነት እና ላስመዘገበው የላቀ አፈፃፀም አመስግነዋል።
ለቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፋይናንስ የማፈላለጉ ሂደት ያለበትን ደረጃ በተመለከተም ለሚስተር ፓንዲ ያብራሩላቸው ሲሆን፤ በዚሁ ዙሪያ ከባንኩ ጋር ቅድመ ውይይት ስለመጀመሩም ጠቅሰውላቸዋል።
የእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ኢነርጂን ጨምሮ ኢትዮጵያ ቅድሚያ ለምትሰጣቸው ቁልፍ የልማት ፕሮጀክቶች ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።
ሚስተር ፓንዲ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እያደረገቻቸው ላሉ የኢኮኖሚ ሪፎርሞች እና መንግሥት ለመሠረተ ልማት ግንባታ ለሰጠው ትኩረት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
የእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር አጋርነቱን ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።
በቢታንያ ሲሳይ
#ebcdotstream #ethiopia #aiib