በኢትዮጵያ አሁን አሁን አዳዲስ ከተሞች እየተመሠረቱ፣ ነባሮቹም በቆዳ ስፋት እና በነዋሪዎች ብዛት እያደጉ መሆኑ በግልጽ ይታያል።
በሀገሪቱ የከተሞች ዓመታዊ የዕድገት ምጣኔ በአማካኝ 5.4 በመቶ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የከተሞች ዕድገት እና መስፋፋት ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የተያያዝ ሲሆን፤ ለአብነትም ቻይና፣ ብራዚል እና አርጀንቲና በዚህ ረገድ በፍጥነት ካደጉ ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት መጽሐፋቸው፥ ከተሞች በባህሪያቸው የሀገራት የሳይንስ፣ የኢኖቬሽን እና የኃይል ዕድገት ማሳለጫ መሆናቸውን ያነሳሉ።
የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ የፖሊሲ አማካሪ ያሬድ ተሾመ (ዶ/ር) ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር ነበራቸው ቆይታ፥ ከተሞች የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳለጫ ይሆኑ ዘንድ 5 ዘርፎች ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ የመደመር መንግሥት መጽሐፍን ዋቤ አድርገው ተናግረዋል።
እነርሱም ኢንዱስትሪያላይዜሽን፣ ኢኖቬሽን፣ ንግድ፣ ሥራ ፈጠራ እና ዲጂታላይዜሽን መሆናቸውን ጠቅሰው፤ እነዚህን ማዕከል ያደረገ ከተማ መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ነባር ከተሞችን የማደስ እና አዳዲስ ከተሞችን የመፍጠር አዲስ የከተማ አተያይ ፖሊሲ እየተከተለች መሆኑን አንስተው፤ በዚህም ተጨማጭ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ለውጦችን ማስመዝገብ መቻሏን አክለዋል።
የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ዘውዱ በበኩላቸው፥ ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን በማድረግ ከተሞችን ለማስተሳሰር እና የአገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ ለማድረግ ስማርት ሲቲን መገንባት ዋነኛ አቅጣጫ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
ይህንኑ የስማርት ሲቲ ፖሊሲ አሁን ላይ ከመዲናዋ አዲስ አበባ አልፎ ክልሎችም ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ሥራ ስለመጀመሩም ነው ያነሱት።
በሜሮን ንብረት
#etv #ebcdotstream #ethiopia #YemedemerMengist #cities #smartcities