Search

ባንኩ ለኢትዮጵያ የሪፎርም አጀንዳዎች ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል - የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ

እሑድ ጥቅምት 09, 2018 43

የአፍሪካ የልማት ባንክ ግሩፕ ለኢትዮጵያ የሪፎርም አጀንዳ ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።
በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የተመራ ልዑካን ቡድን ከዓለም ባንክ እና አይ ኤም ኤፍ ዓመታዊ ስብሰባዎች ጎን ለጎን ከአዲሱ የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዚዳንት ሲዲ ኦዉልድ ታህ (ዶ/ር) ጋር በስትራቴጂያዊ አጋርነትና የሁለትዮሽ ትብብርን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በአሜሪካ ዋሺንግተን ውይይት አድርገዋል።
 
በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ እና የኢንቨስትመንት ሥራዎችን ምቹ ለማድረግ፣ ቁልፍ በሆኑ ዘርፎች ምርታማነትን ለማሳደግ እና የመንግሥትን የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን እየተሰሩ ባሉ የሪፎርም ሥራዎች ላይ ለፕሬዚዳንቱ ገለፃ ተደርጎላቸዋል።
ለቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክት መሪ የፋይናንስ አፈላላጊ በመሆን ስምምነት ያደረገው ባንኩ በዚሁ ሥራ ላይ የበኩሉን ድርሻ መወጣት በሚችልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል።
የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ እና ሌሎች ትላልቅ የሪፎርም አጀንዳዎችን አፈፃፀም ያደነቁት ሲዲ ኦዉልድ ታህ (ዶ/ር) ባንኩ የሀገሪቱን ግዙፍ የለውጥ አጀንዳዎችን በመደገፍ ፣ በግብርና እና በመሰረተ ልማት ላይ ኢንቨስት በማድረግ በተለይም የአየር ትራንስፖርት ትስስርን በማጠናከር፣ የቀጣናዊ ትስስርና የኢኮኖሚ ውህደት እንቅስቃሴዎች ላይ ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ በበኩላቸው ሲዲ ኦዉልድ ታህ (ዶ/ር ) የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዚዳንት ሆነው በመመረጣቸው የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል።
በባንኩ በሚኖራቸው አመራር ዘመን ውጤታማ እንደሚሆኑ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ገልፀው፤ ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙም የገንዘብ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
 
በላሉ ኢታላ