ኢትዮጵያ የተትረፈረፈ ኃብት ምድር ናት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው፤ በባሌ ዞን ከተለያዩ አመራሮች ጋር ያደረግነው ጉብኝት የመጨረሻ መዳረሻ አስደማሚው የፊንጫ ሀበራ ፏፏቴ ሆኗል ብለዋል።
በግርማ የሚወርደው ፏፏቴ ወደ ሶፍኡመር የዋሻ ሥርዓት የሚደመረውን የወይብ ወንዝ የሚቀላቀል መሆኑንም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮ የሚገኝበት ይኽ አስደናቂ ከባቢ ድንቅ የአዕዋፍ መገኛና በቅርቡ የዋሻ መስህብ የተገኘበት እንዲሁም የራፉ ውብ የዐለት ደን አቅራብያ የሚገኝ ነው ብለዋል።
በአካባቢው የሚገነባው ማረፊያ በቅርቡ ሲጠናቀቅ ለጎብኝዎች የበለጠ ሳቢ እና ምቹ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
በኃብት ስጦታ አንፃር ስንመለከት ኢትዮጵያ ለሁሉም የሚበቃ ኃብት እንዳላት እናውቃለን ሲሉም አመልክተዋል።
ባለፉት ሶስት ቀናት በጉብኝቱ የተሳተፉ የቀድሞ እና በሥራ ላይ ያሉ ኃላፊዎች በጉብኝቱ የተመለከቱት የተፈጥሮ፣ የባሕል እና የሰው ኃብት ከፍ ያለ መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው ጠቅሰዋል።
የጋራ ሥራችን እነዚህን ኃብቶቻችንን መግለጥ፣ ማሳደግ፣ በኃብቶቹ ላይ በመጨመር ቀጣዩ ትውልድ ችቦውን ተረክቦ እንዲቀጥል መሠረት መጣል ነው ሲሉም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በርግጥም የተትረፈረፈ ኃብት ምድር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እንሰባሰብ፣ ለማለም እንድፈር፣ የጋራ ነጋችንን በጋራ እንገንባ ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #AbiyAhmedAli #bale