በዓለም ታሪክ ውስጥ የሀገር ክህደት ወይም ባንዳነት ሥር የሰደደ እና ሀገርን ለውጭ ኃይሎች አሳልፎ የመስጠት ጥቁር ጠባሳ ነው። ታሪክ ደግሞ ለዚህ ተግባር የሚሰጠው ምላሽ ሁልጊዜም አንድ ዓይነት ነው፤ ውርደት እና ፍጹም ኪሳራ።
ባንዳነት መጀመሪያ ላይ ለሕዝብ ነጻነት እና ጥቅም የሚል የሐሰት ጭንብል ቢኖረውም፣ በተግባር ግን የውጭ ኃይሎችን ፍላጎት በማስፈጸም የሀገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል መርዛማ ፍሬ ነው።
ለዚህም በዓለም ታሪክ ውስጥ የተመዘገቡት የከዳተኞች ፍጻሜ ማሳያ ነው። የፈረንሳዩ ማርሻል ፊሊፕ ፔታን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ናዚ ጀርመን ፈረንሳይን በወረረችበት ወቅት ከጠላት ጋር በመተባበር ደካማ መንግሥት በመመሥረት የፈረንሳይ አይሁዶችን እና የሀገሪቱን ሀብት ለጀርመን አሳልፎ ሰጠ።
ናዚ ሲሸነፍ ፔታን በሀገር ክህደት ወንጀል ተከስሶ የሞት ፍርድ ተፈረደበት፤ በኋላም በእስራት ዓለምን በውርደት ተሰናበተ።
የኖርዌዩ ቪድኩን ኩዊዝሊንግ ጀርመን ኖርዌይን ስትወርር የገዛ ሀገሩ መከላከያ ጦር እጁን እንዲሰጥ ጥሪ ያቀረበ እና የናዚ ተላላኪ መሪ የነበረ ሲሆን፣ ኖርዌይ ነጻ ስትወጣ ወዲያውኑ በቁጥጥር ሥር ውሎ በጥይት ተደብድቦ ተገደለ። ዛሬም ድረስ በብዙ ቋንቋዎች “ኩዊዝሊንግ” (Quisling) የሚለው ቃል የከዳተኛ ቀጥተኛ ትርጉም ነው።
የቻይናው ዋንግ ጂንግዌይም ጃፓን ቻይናን በወረረችበት ወቅት ደካማ መንግሥት በማቋቋም በወገኖቹ ላይ የሚፈጸመውን ጭፍጨፋ በዝምታ ተመለከተ።
ጦርነቱ ሳያልቅ በሕመም ቢሞትም፣ የቻይና ሕዝብ ቁጣ ስላልበረደ ከሞተ በኋላ መቃብሩ ተቆፍሮ አስከሬኑ እንዲቃጠል እና የመታሰቢያ ሐውልቱ እንዲፈርስ ተደርጓል።
እነዚህ ምሳሌዎች የሚያረጋግጡት የውጭ ደጋፊዎቻቸው ሲሸነፉ ወይም ጥቅማቸው ሲያበቃ ባንዳዎች የሚጠለሉበት ቦታ አጥተው በታሪክ ማኅደር በጥቁር ነጥብ ተመዝግበው እንደሚያልፉ ነው።
ይህ እውነታ በኢትዮጵያ ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ሂደት ውስጥም ግልጽ መልክ አለው። በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ወቅት የነበሩት የሀገር ውስጥ ባንዳዎች ለግል ጥቅም፣ ለሥልጣን ማዕረግ እና ለቁሳዊ ማባበያ ሲሉ ከውጭ ወራሪዎች ጋር በማበር የገዛ ወገኖቻቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል።
ወራሪው ኃይል የብሔር እና የሃይማኖት ልዩነቶችን በመጠቀም ሕዝቡን ለመከፋፈል እና የውስጥ ክፍተቶችን ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት አድርጎ ነበር። ይሁን እንጂ ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀውን የጠላት ጦር እና የውስጥ ተላላኪዎችን ያሸነፈው የዐርበኞች እና የሕዝቡ የጸና አንድነት ነው።
ዐርበኞቹ በሕዝቡ ሁለንተናዊ ድጋፍ፣ ስንቅ በማቀበል እና መረጃ በመስጠት ረገድ ጋሻ እና መከታ ሲሆኑ፣ ባንዳዎች ግን በማኅበራዊ መገለል እና በሞራል ኪሳራ በገዛ ወገኖቻቸው ዘንድ መሸሸጊያ አጥተዋል።
ፋሺስት ጣሊያን ድል ተመትታ ሀገር ለቅቃ ስትወጣም አብረዋቸው የሠሩትን ባንዳዎች ሜዳ ላይ ጥለዋቸው መሄዷ፣ የውጭ ኃይሎች ለባንዳዎች ያላቸው አመለካከት በጊዜያዊ ጥቅም ላይ ብቻ የተመሠረተ እንጂ ቋሚ ወዳጅነት እንደሌላቸው ትልቅ ማሳያ ነው።
ዛሬም ቢሆን የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ፣ ጂኦ-ፖለቲካዊ እና ታሪካዊ ዕድገት የማይፈልጉ የውጭ ኃይሎች የውስጥ ክፍተቶችን በመጠቀም ሀገራችንን ለማዳከም ይጥራሉ።
በአሁኑ ወቅት የዛሬዎቹ የውስጥ ተላላኪዎች እና የውጭ ኃይሎች ተቀናጅተው በሀገራችን ላይ ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖ በመፍጠር ብሔራዊ ጥቅሟን ለመጉዳት እየሠሩ ይገኛሉ።
ይህ ቅንጅት በዋናነት የሀገርን የኢኮኖሚ እና የልማት ምሰሶዎች ማዳከምን ዓላማ ያደረገ ሲሆን፣ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፍጻሜውን እንዳያገኝ፣ ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች እንዳይሳኩ እና የሀገራችን የስትራቴጂካዊ ሕልውና ጥያቄ የሆነው የባሕር በር መዳረሻ ጥረት እንዲደናቀፍ በጋራ ይሠራሉ።
ለዚህም ስኬት የውጭ ኃይሎቹ የፋይናንስ፣ የዲፕሎማሲ እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ሲያቀርቡ፣ የውስጥ ተላላኪዎቹ ደግሞ የብሔር እና የሃይማኖት ፅንፈኝነትን በማቀጣጠል፣ በሕዝቦች መካከል መጠራጠርን በመዝራት እና የፀጥታ ቀውሶችን በመፍጠር የሀገርን መረጋጋት ለማናጋት ይተጋሉ።
በተለይም የግብጽ የዘመናት ስትራቴጂ በምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ የበላይነቷን ለማረጋገጥ እና የዓባይን ውኃ እንዳንጠቀም ለማደናቀፍ፣ እነዚህን የውስጥ ቅሬታዎች እና ተከፋይ ቡድኖች እንደ መሣሪያ ይጠቀማል።
እነዚህ ኃይሎች በተቀነባበረ ዘመናዊ የሚዲያ እና የሳይበር ዘመቻ፣ ሀገር የሚያፈርሱ እና የሕዝብን ሰላም የሚነሡ ቡድኖችን እንደ ዐርበኛ በመሣል፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ጫናዎችን በመፍጠር እና በሰብአዊ ዕርዳታ ስም የውስጥ ጣልቃ ገብነት እና የሎጂስቲክስ ድጋፍ በመስጠት አፍራሽ ሚናቸውን ይጫወታሉ።
ዓላማቸውም ኢትዮጵያን ያልተረጋጋች፣ የፀና መንግሥት የሌላት እና በድህነት የምትማቅቅ ደካማ ሀገር ማድረግ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያውያን ፅናት እና ቁርጠኝነት ግን ሁልጊዜም ስልታቸውን ያከሽፈዋል።
በመሆኑም የባንዳነት እና የውጭ ጣልቃ ገብነት ሴራዎችን ሙሉ በሙሉ ለማክሸፍ የዜጎችን ንቃት ማሳደግ፣ ማኅበረሰቡ የሚነዙ የውጭ ፕሮፓጋንዳዎችን በጭፍን ከመቀበል ይልቅ የሴራዎቹን ምንጭ እና ዓላማ ለይቶ እንዲያውቅ ማስተማር ወሳኝ ነው።
ከዚህ ጎን ለጎን የሀገር ውስጥ የደኅንነት መዋቅርን ማጠናከር፣ በሰብአዊ ዕርዳታ ስም በሚገቡ ቁሳቁሶች ላይ ጥብቅ የድንበር እና የሎጂስቲክስ ቁጥጥር ማድረግ እንዲሁም በተለዋዋጭ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ውስጥ ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ያደረገ፣ መርሕን ያስቀደመ ፖለቲካዊ ብስለት እና ፕራግማቲክ ዲፕሎማሲ ማሳየት ያስፈልጋል።
ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ከፋፋይ እና ነጠላ ትርክቶችን በማስወገድ፣ በጋራ መከባበር እና በመደመር እሳቤ ላይ የተመሠረተ ጽኑ የወል ትርክት መገንባት ለዘላቂ ሰላም፣ ልማት እና ሁለንተናዊ ብልጽግናዋ ዋነኛው መፍትሔ ነው።
ታሪክ እንደሚመሰክረው የኢትዮጵያ ክብር እና ሉዓላዊነት በታማኝ ልጆቿ መሥዋዕትነት እና በዐርበኝነት እሴቶች የሚፀና ሲሆን፣ የግል ጥቅም እና የሥልጣን ጥምን አስቀድመው ከውጭ ኃይሎች ጋር የሚተሣሠሩ ተላላኪዎች ፍጻሜ ግን ውድቀት እና የታሪክ ተወቃሽነት ነው።
ስለሆነም አንድነቷ የተጠበቀ እና ብልጽግናዋ የተረጋገጠ ሀገር ለቀጣይ ትውልድ ማሸጋገር፣ የባዕዳን ኃይሎች እና የተላላኪዎቻቸው የመጨረሻ ኪሳራ ይሆናል።
በበረከት ሽመልስ