የዩናይትድ ኪንግደም በአፍሪካ አህጉር ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውለውን፣ የላቀ የሰነድ ማጭበርበር (ፎርጀሪ) መመርመሪያ የኤቪዬሽን ደኅንነት ቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አበርክታለች።
በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ዳረን ዌልች በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት፣ ይህ የቴክኒክ ድጋፍ የሁለቱን ሀገራት የጠበቀ ወዳጅነት እና ስትራቴጂያዊ አጋርነት በግልጽ የሚያሳይ ነው።
በእንግሊዝ ሀገር የተመረተው ይህ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ተግባራዊ መደረጉንም አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።
ይህም ዩናይትድ ኪንግደም በኢትዮጵያ የደኅንነት አቅም ላይ ያላትን ሙሉ እምነት የሚያረጋግጥ መሆኑን አክለዋል።
ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቁልፍ የዓለም አቀፍ መተላለፊያ ማዕከል መሆኑን ያነሱት አምባሳደሩ፣ የተቋሙ አመራሮች እና ሠራተኞች የእንግሊዝ ዜጎችን ጨምሮ የዓለምን ማኅበረሰብ ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያደርጉትን የላቀ ጥረት አድንቀዋል።
"ሁላችንም ደኅንነታችን እስካልተረጋገጠ ድረስ የማንም ደኅንነት የተጠበቀ አይሆንም" በማለትም የጋራ ደኅንነትን ፅንሰ-ሀሳብ አስምረውበታል።

ይህ የቴክኖሎጂ ድጋፍ እና ትብብር ድንበር ዘለል የተደራጁ ወንጀሎችን ለመከላከል እንዲሁም የጉዞ መስመሮችን ከሕገ-ወጥ ድርጊቶች ነጻ ለማድረግ የላቀ ሚና ይጫወታል።
አምባሳደሩ እንዳብራሩት የሁለቱ ሀገራት አጋርነት በደኅንነት ዘርፍ ብቻ ሳይወሰን፤ በጤና፣ በትምህርት እና በኢኮኖሚ ልማት ጭምር ሰፊ መሠረት ያለው ነው።
በቀጣይም በቢሾፍቱ በሚገነባው አዲስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዲዛይን እና ግንባታ ላይ የራሳቸውን ድርሻ ለመወጣት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል::

አውሮፕላን ማረፊያው በዓለም ላይ ካሉ ደኅንነታቸው እጅግ ከተጠበቁ ተርሚናሎች አንዱ እንዲሆን በጋራ ለመሥራት ዩናይትድ ኪንግደም ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላትም አምባሳደሩ ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ ወደ ሂትሮው፣ ማንችስተር፣ ጋትዊክ እና ግላስኮ የሚደረጉ ዕለታዊ እና መደበኛ በረራዎች የሁለቱን ሀገራት የንግድ እና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ይበልጥ እያሳደጉት መሆኑን አምባሳደሩ አንስተዋል።
የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጠው ይህ የደኅንነት ትብብር ውጤታማነቱ ታይቶ በቀጣይም ተጨማሪ የቴክኖሎጂ ድጋፎች እንደሚደረጉ አመላክተዋል።