Search

ነገን እየፈጠረ ያለ ትውልድ - የዘመን ዝላይ እና የመደመር አብርሆት

ረቡዕ ሰኔ 10, 2018 71

የሀገራት ሥልጣኔ እና ታላላቅ የድል ትርክቶች፣ በታሪክ ሰንሰለት ውስጥ በየዘመናቱ በሚነሡ ድንቅ ትውልዶች ትከሻ ላይ ይገነባሉ።

ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ምድር ታሪክን እየቀየረ ያለ፣ ታላቅ እና ነገን ዛሬ ላይ እየፈጠረ ያለ አዲስ ትውልድ እየተነሣ መሆኑን እንገነዘባለን።

ይህ "የመደመር ትውልድ" ይባላል፤ የትናንትናውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ዕዳ በብልሃት እያወራረደ፣ በዛሬው መሠረት ላይ ለነገዋ ሀገር የድል ድልድይ እየገነባ ያለ የተግባር ትውልድ ነው።

ትውልዱ ከስህተቶች እየተማረ፣ ያለፈውን ቁስል በአብሮነት ፈውስ እየተካ የብልጽግናን ጉዞ በማፋጠን ላይ ይገኛል።

ይህ ትውልድ በሥነ ልቦናዊ ጥንካሬው እና በውስጣዊ ጽናቱ ወደር አይገኝለትም። ዘመናት ያወረሱትን የልዩነት አስተሳሰብ ተሻግሮ፣ በትልቅ ደረጃ የማሰብ የሥነ ልቦና ልዕልናን ተላብሷል።

ፈተናዎች ሲበዙበት የማይዝል፣ ውጣ ውረዶች ሲያጋጥሙት ይበልጥ የሚጠነክር የማይበገር መንፈስ አለው። የትናንትን ሸክም በአሸናፊነት መንፈስ እያራገፈ፣ አዳዲስ ሐሳቦችን በማመንጨት ሀገራዊ አንድነትን ከልማት ጋር ያሰናስላል። ጥንካሬው፣ ትውልዱን ሩቅ አሻግሮ እንዲመለከት እና ለታላቅ ራዕይ እንዲተጋ አድርጎታል።

ይህ የሥነ ልቦና ልዕልና ከዘመኑ ዕውቀት እና ቴክኖሎጂ ጋር ሲዋሐድ አቅሙን እጥፍ ያደርገዋል። ትውልዱ በዝግታ ማዝገምን በመተው በዘመን ዝላይ (Leapfrog) ከጊዜ እና ስፍራ ዑደት ጋር እየተዋጋ፣ የዛሬዋን ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የዲጂታል አውድ ጋር በእጅጉ እያስተሳሰረ ይገኛል።

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን፣ የዳታ ሳይንስን እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን መሣሪያው በማድረግ፣ ሀገሩን በፈጠራ ወደፊት ያመጥቃል። የዘመኑን ዕውቀት በአቋራጭ በመቀበል፣ ከሀገሩ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ያጣጥማል።

ይህን ታላቅ ንቅናቄ በዓለም ታሪክ ከተመዘገቡት ታላላቅ የንቃት ዘመናት ጋር ማነጻጸር ትልቅ ትርጉም ይሰጠናል።

14ኛው ክፍለ ዘመን በጣሊያን ፍሎረንስ የፈነጠቀው የሕዳሴ (Renaissance) ዘመን፣ አውሮፓን ከጨለማው ዘመን አውጥቶ ወደ ጥበብ እና ሳይንስ ልዕልና እንዳሸጋገራት ታሪክ ይመሰክራል።

 

 

 

 

 

 

 

ልክ እንደ ፍሎረንሱ ሕዳሴ፣ ይህ የመደመር ትውልድም የኢትዮጵያን የሕዳሴ ብርሃን እያበራ፣ አዲስ የፈጠራ እና የሥራ ባህልን እየዘራ ነው። ነባሩን ዕውቀት ከአዲሱ ጋር በማዋሐድ አዕምሯዊ ልደት ያመጣል።

18ኛው ክፍለ ዘመን እንደታየው የአውሮፓ የአብርሆት (Enlightenment) ትውልድ፣ የዛሬው የኢትዮጵያ ወጣትም በምክንያታዊነት፣ በዕውቀት እና በሳይንስ ላይ የተመሠረተ የማሰብ አድማስን ከፍቷል።

የአውሮፓ አብርሆት የነጻ አስተሳሰብን እንዳጸና ሁሉ፤ የመደመር ትውልድ ደግሞ የቴክኖሎጂን ዝላይ ከሀገር በቀል እሴቶች እና ከአብሮነት ፍልስፍና ጋር በማዋሐድ ልዩ የኢትዮጵያ አብርሆት በተጨባጭ እየፈጠረ ይገኛል። ይህም ሀገራችንን ከኋላ ቀርነት አላቅቆ ወደ ዘመናዊነት ያስፈነጥራል።

በመሆኑም፣ ይህ ትውልድ የኢትዮጵያ ቀኝ የሆነ፣ ጊዜው የጠየቀውን ታላቅ ሀገራዊ ተልዕኮ በአግባቡ የተረዳ መሪ ትውልድ ነው። የትናንትን ዕዳ ከፋይ ብቻ ሳይሆን፣ የነገን ብልጽግና ጀማሪ፤ የችግሮች ተንታኝ ብቻ ሳይሆን፣ የመፍትሔዎች ፈጣሪ ነው። በላቀ የሥነ ልቦና ጥንካሬ ሀገሩን ወደ ታላቅ ከፍታ ያሻግራል።

አዎ! የኢትዮጵያ ቀኝ የሆነ ታላቅ ትውልድ መነሣቱን ዛሬ በኩራት መናገር እንችላለን። በዘመኑ ዕውቀት ታጥቆ፣ የመደመርን እሴት በልቡ አትሞ፣ የነገዋን ገናና ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ እየፈጠረ ያለ ድንቅ ትውልድ ነው።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ