Search

የባሕር በር፦ የኢትዮጵያ የሉዓላዊነት እና የኅልውና ጋሻ

ረቡዕ ሰኔ 10, 2018 65

ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለ ገደብ የተሰጣት የተፈጥሮ ፀጋ፣ የጀግንነት ታሪክ እና ግዙፍ የሕዝብ ቁጥር ያላት የምስራቅ አፍሪካ ምሰሶ ናት።

ኢትዮጵያ በታሪክ ማኅደሯ ውስጥ ትልቅ ጂኦ-ፖለቲካዊ እንቆቅልሽ ይዛ ትጓዛለች። ይህ እንቆቅልሽም እስካሁን ያልተፈታው የባሕር በር ጉዳይ ነው።

የባሕር በር ለኢትዮጵያ እንዲሁ የውሃ አካል ወይም የንግድ መስመር ብቻ አይደለም፤ የብሔራዊ ደኅንነት፣ የኢኮኖሚ ነፃነት እና የጥንታዊ ሥልጣኔዋ ትንሳኤ ማረጋገጫ ጭምር ነው።

በአፍሪካ ቀንድ እምብርት ላይ የምትገኘው ይህች ጥንታዊት ሀገር ባሕር በር አልባ መሆኗ፣ በሉዓላዊነቷ እና በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷ ላይ ያጠላው ጥላ ከባድ ነው።

ሀገራችን በታሪካዊ ስህተት ያጣችውን የባሕር በር ባለቤትነት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማስመለስ፣ ይህን ታሪካዊ ስህተት ለማረም እና ለትውልድ የሚተርፍ የስትራቴጂ ማዕቀፍ ለመቅረጽ ቀንና ሌሊት እየሠራች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት ያስመዘገበችውን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በዘላቂነት ለማስቀጠልና ወደ ላቀ የኢንዱስትሪ ምዕራፍ ለመሸጋገር አስተማማኝ የሆነ የራሷ የባሕር በር ያስፈልጋታል።

ሀገራችን በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለወደብ ኪራይና ለአገልግሎት እየከፈለች መኖሯ ስትራቴጂያዊ እስር ቤት ሆኖባት ቆይቷል። ከዚህም አልፎ ጉዳዩ ሉዓላዊነቷን የሚፈታተን ሆኗል::

ቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረ ሰላጤ የዓለም ንግድና የኃይል አቅርቦት ዋነኛ መተላለፊያ መስመሮች በመሆናቸው፣ የዓለም ኃያላን ሀገራት ጦር ሰፈሮቻቸውን በቀጣናው ገንብተዋል።

በዚህም የክልላዊ ኃይሎች የጥቅም ግጭት፣ የሕጋዊነት ጥያቄዎች እና የጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች በኢትዮጵያ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን ሲፈጥሩ ቆይተዋል።

በመሆኑም ሀገራችን የባሕር በር ባለቤትነቷን ለማረጋገጥ የምትጓዝባቸው መንገዶች እጅግ ጥንቃቄ የተመላባቸው እና ዓለም አቀፍ ሕግጋትን ያከበሩ ናቸው።

የባሕር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያ የቅንጦት ወይም ለፖለቲካ ፍጆታ የሚነሳ ጥያቄ አይደለም፤ ይልቁንም የኅልውና፣ የብሔራዊ ኩራት እና የኢኮኖሚ ነፃነት ማረጋገጫ ድልድይ ነው።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ተሰሚነት ለማሳደግ፣ የዲጂታልና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ለማወጅ እና ወደ ፊት ለምትገነባው ጠንካራ ሀገር መሠረት ለመጣል የባሕር በር ባለቤት መሆን አማራጭ የሌለው ግብ ነው።

በንፍታሌም እንግዳወርቅ