Search

ድህነትን የምናሸንፍበት የጋራ ቀመራችን፡ "መደመር"

ረቡዕ ሰኔ 10, 2018 80

ትናንት ኢትዮጵያዊያን በአንድነት እና በትብብር ጸንተው በመቆማቸው ነበር ታሪካዊውን የዓድዋ ድል ለዓለም ያበሰሩት።

የዓድዋ ድል የተገኘው በወታደራዊ አቅም የበላይነት ብቻ ሳይሆን በመደመር ኃይል፣ በሀገር ፍቅር ስሜት እና ሀገርን ከጥፋት ለመታደግ በተደረገ ጽኑ ሕዝባዊ ትብብር ነበር።

ዛሬም ኢትዮጵያ እንደ ድህነት፣ ረሃብ እና ጉስቁልና ያሉ ታሪካዊ ጠላቶችን ድል ለማድረግ፣ ያንን የዓድዋ የትብብር እና የአንድነት መንፈስ ዳግም ማነቃቃት ይኖርባታል።

በትናንትናው ታሪካችን ወራሪን በዓድዋ ድል እንዳደረግነው ሁሉ ዛሬም በመደመር መንገድ ላይ በአንድ ልብ በመሰባሰብ ድህነትን እና ኋላ ቀርነትን በጋራ ድል በማድረግ ወደ ብልፅግና ማማ መሻገር እንችላለን።

ማንኛውም ሀገር ካለበት የድህነትና የኋላ ቀርነት አረንቋ ወጥቶ የብልፅግና ማማ ላይ መውጣት የሚችለው የዜጎችን ልብ፣ ዕውቀት እና አቅም በአንድነት ማሰባሰብ ሲችል ነው።

ታሪካዊ ፈተናዎችን በጋራ የመሻገር ታላቅ ተሞክሮና ኩራት ያላት ሀገራችን ዛሬም የነገ ተስፋዋን ለማለምለም እና ካለችበት ውስብስብ ወቅታዊ ፈተና ለመውጣት አዲስ የጋራ አስተሳሰብ ያስፈልጋታል።

ይህንን ሀገራዊ ተስፋ እውን ለማድረግ ደግሞ "መደመር" ሁሉንም ለአንድ ታላቅ ዓላማ የሚያሰባስብ ዋነኛው መፍትሔ ሆኖ ቀርቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) "የመደመር መንገድ" በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ፣ "ከድህነት ማዶ አሻግሮ ወደ ብልጽግና ጎዳና የሚያስገባን ትክክለኛ መንገድ መለያየት ሳይሆን መተባበር ነው፤ መበታተን ሳይሆን መሰባሰብ ነው" ይላሉ።

ይህ ሀሳብ የኢትዮጵያ የነገ ተስፋ እና ስኬት መሠረታዊ ፍልስፍና፣ ብሎም መሪ መንገድ ነው።

የመደመር እሳቤ በሀገራችን ያሉትን ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፈተናዎች ተቋቁመን አዲስ እና ብሩህ ምዕራፍ ለመክፈት የሚያስችል ተግባራዊ ፍልስፍና ነው።

 

ፍልስፍናው የሀገር ውስጥ አቅምን እና የሕዝብን ማኅበራዊ ካፒታል በማቀናጀት፣ ልዩነቶችን ወደ ውበት እና ወደ ጥንካሬ በመቀየር ላይ ያተኩራል።

ከመለያየት ይልቅ መተባበርን፣ ከመበታተን ይልቅ መሰባሰብን ዋና መርሁ በማድረግ ሀገራችንን ወደ ተሟላ ብልጽግና የሚያሸጋግር አስተማማኝ ጎዳና ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች የጀመረቻቸው መጠነ ሰፊ የልማት እና የሰላም ጉዞዎች እጅግ የላቀ የሕዝብ ትብብርን እና አብሮነትን ይሻሉ።

በአሁኑ ወቅት ሀገራችን የምታካሂዳቸው ግዙፍ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ጥረቶች፣ የአረንጓዴ አሻራ እና የከተማ ኮሪደር ልማቶች የዚህ ፍልስፍና ማሳያ ናቸው።

እነዚህ ታላላቅ ፕሮጀክቶች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጉልበታቸውን፣ ዕውቀታቸውን እና ገንዘባቸውን በጋራ "የደመሩባቸው" የድል አደባባዮች ናቸው።

እነዚህ ሁሉ ስኬታማ ሊሆኑ የሚችሉት እና ዘላቂነታቸው የሚረጋገጠው የመላው ኢትዮጵያውያን ሁለንተናዊ ድጋፍና ትብብር ይበልጥ ሲታከልበት ነው።

በተመሳሳይ መልኩ ዘላቂ ሰላምን እና ደኅንነትን ለማረጋገጥ የሚደረጉት ሀገራዊ የምክክር እና የዕርቅ ጥረቶች ሁሉ ሕዝብን በማሰባሰብ እና በመደመር ላይ የተመሠረቱ ናቸው።

ልማት እና ሰላም ያለ ትብብር ሊታሰቡ የማይችሉ በመሆናቸው፣ አሁን የተያያዝናቸውን ስኬቶች ለማስቀጠል እና አዳዲስ ዕድሎችን ለመጠቀም ሁላችንም በአንድነት እና በጋራ መቆም አለብን።

በለሚ ታደሰ