የተፈጥሮ እና ሥነ-አካባቢ ጥበቃ በቀላል ዘመቻ የሚረጋገጥ ሳይሆን፣ ጥልቅ ራዕይን፣ ሳይንሳዊ አሠራርን እና የተቀናጀ የትግበራ ስልትን የሚጠይቅ ዘርፈ-ብዙ የትውልድ አደራ ነው።
በኢትዮጵያ በተግባር እየታየ ያለው "የአረንጓዴ ዐሻራ" መርሐ-ግብር ከዚህ አንጻር ሲገመገም፣ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትልቅ ተሞክሮ የሚሆንበት ዐቢይ ምክንያት የተመራበት የተቀናጀ አግባብ ነው።
ይህ ግዙፍ ሀገራዊ እና አህጉራዊ ፋይዳ ያለው የሥነ-ምኅዳር ተሃድሶ ፕሮግራም ስኬታማ ሊሆን የቻለባቸውን መሠረታዊ የአመራር እና የትግበራ እርከኖች በሚከተለው መልኩ መመልከት ይቻላል፦
የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና ራዕይ
በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማ የሆኑ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች በሙሉ ከከፍተኛው የፖለቲካ አመራር ጽኑ ቁርጠኝነትን ይፈልጋሉ።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብርም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት መጀመሩ እና በቀጥታ አመራር ሰጪነት መመራቱ፣ ጉዳዩ ወቅታዊ አጀንዳ ብቻ ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ያሳያል።
ይህ ከፍተኛ የፖለቲካ ድጋፍ ሀገራችን ያላትን ሀብት፣ የሰው ኃይል እና ጊዜ በአንድ ማዕከል አስተባብራ ወደ ተግባር እንድትገባ ትልቁ ሞተር ሆኗታል።
ተቋማዊ ቅንጅት
የሥነ-አካባቢ ጉዳይ የአንድ ተቋም ወይም ሚኒስቴር ኃላፊነት ብቻ አይደለም፤ የውኃ፣ የግብርና፣ የፋይናንስ፣ የትምህርት እና የሚዲያ ተቋማትን ሰፊ ርብርብ ይጠይቃል።
በአረንጓዴ ዐሻራ አፈጻጸም ሂደት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መናበባቸው፣ የግብዓት አቅርቦት እንዳይስተጓጎል፣ የመረጃ ልውውጥ የተሳለጠ እንዲሆን እና የክትትል እና ግምገማ ሥርዓቱ ጠንካራ እንዲሆን አስችሏል። ይህ ቅንጅታዊ አሠራር ብክነትን በመቀነስ የውጤታማነት ምጣኔውን ከፍ አድርጎታል።
መልክዓ-ምድራዊ ውክልና እና የሥልጣን ውክልና
ኢትዮጵያ እጅግ የተለያየ እና ሰፊ የሥነ-ምኅዳር ዞኖች ያላት ሀገር ናት። ስለሆነም ማዕከላዊ ዕቅዱን ወደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ቀይሮ መተግበር ያስፈልጋል።
የክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮች እና የሴክተር መሥሪያ ቤቶች የሥራው ዋነኛ አስፈጻሚ መሆናቸው፣ በየአካባቢው ያለውን የአየር ንብረት፣ የአፈር ዓይነት እና የኅብረተሰብ ፍላጎትን ያማከለ የችግኝ ተከላ እንዲከናወን አድርጓል።
ይህ አግባብ ትክክለኛውን ዛፍ በትክክለኛው ቦታ ለመትከል የሚያስችለውን መርሕ ተግባራዊ ለማድረግ ወሳኝ ነው።
ሳይንሳዊ እና ቴክኒካዊ ድጋፍ
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን ማዘጋጀት፣ ማጓጓዝ እና መትከል ከፍተኛ የሆነ የቴክኒክ ክህሎት ይጠይቃል። ከችግኝ ጣቢያ ዝግጅት እስከ ዘር ምርጫ፣ እንዲሁም ከተከላ ቦታ ልየታ እስከ እንክብካቤ ድረስ ያለው ሂደት በዘፈቀደ ሳይሆን በየደረጃው በተዋቀሩ የቴክኒክ ኮሚቴዎች መመራቱ የፕሮግራሙን ሳይንሳዊ መሠረት አጠንክሮታል።
ኮሚቴዎቹ የችግኞችን የመፅደቅ ምጣኔ ለመጨመር የሚያስችሉ የሙያ ምክሮችን ከመስጠት ባሻገር፣ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲሰጥ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።
የተደራጀ የሕዝብ ተሳትፎ
የማንኛውም የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ዘላቂነት የሚረጋገጠው ማኅበረሰቡ ሲቀበለው እና ሲሳተፍበት ነው።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ከልሂቃን እስከ አርሶ አደር፣ ከወጣቶች እስከ አዛውንቶች በንቃት የተሳተፉበት ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።
ይህ የተደራጀ የሕዝብ ተሳትፎ፣ ማኅበረሰቡ በሚተከሉ ችግኞች እና በአካባቢው ላይ ጥልቅ የሆነ የባለቤትነት ሥነ-ልቦና እንዲገነባ አድርጓል።
ሕዝቡ ራሱ የተከለውን ዛፍ እንዲንከባከብ፣ የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ እና የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅማችን እንዲጎለብት መሠረት ጥሏል።
የአረንጓዴ ዐሻራ ተነሣሽነት በዓለም አቀፍ ደረጃ በስኬት ከሚጠቀሱ አረንጓዴ ፕሮጀክቶች ተርታ እንዲሰለፍ ያደረገው ከላይ የተዘረዘረው ባለ አምስት ምሰሶ የተቀናጀ አግባብ ነው።
ከከፍተኛ የፖለቲካ አመራር ተነሥቶ፣ በተቋማት ቅንጅት ታጅቦ፣ በሳይንሳዊ የቴክኒክ አሠራር ተደግፎ ወደ ሕዝብ የወረደው ይህ እንቅስቃሴ፤ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሚዛኗን ጠብቃ ለቀጣዩ ትውልድ አረንጓዴ እና የበለጸገች ሀገር ለማስረከብ የምታደርገውን ጉዞ የሚያፋጥን ነው።
በዮናስ በድሉ