የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላት ወርቅ ኃይሉ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፥ በአሁኑ ወቅት የሁሉም የምርጫ ክልሎች ውጤቶች ወደ ማዕከል ገብተው የቆጠራ ማጠናቀቂያ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በማረጋገጡ ሂደት ላይ ትልቅ ኃላፊነት ተወስዶ ቀን እና ሌሊት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ሰብሳብዋ አብራርተዋል::

እንደ ሰብሳቢዋ ማብራሪያ፤ ከ1 ሺህ 139 የምርጫ ጣቢያዎች መካከል የ501 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የ638 የክልል ምክር ቤት ውጤቶች ተጠቃልለው ወደ ማዕከል ገብተዋል።

ከእነዚህ ውስጥም 723ቱ በቦርዱ ፀድቀው ወደ መረጃ ቋት እየገቡ ይገኛሉ ብለዋል ወ/ሮ ሜላትወርቅ።
በተጨማሪም የ253 የምርጫ ጣቢያዎች ውጤት የማረጋገጥ እና የኦዲት ሥራ ተከናውኖ ለቦርዱ ለመቅረብ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ይህን የማጣራት ሥራ በላቀ ጥንቃቄ ለማከናወን የውጤት አረጋጋጭ ባለሙያዎች መረጃዎችን ወደ ኦዲት ክፍል በመላክ የመጨረሻ ማረጋገጫ እያደረጉ መሆኑን አክለው ገልጸዋል።
በለሚ ታደሰ