አረንጓዴው አብዮት፤ ከችግኝ ተከላ እስከ ሀገር ግንባታ
በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከተለመደው የዛፍ ተከላ ዘመቻ ባለፈ፣ የሀገርን ሁለንተናዊ ገፅታ እና ዲፕሎማሲያዊ መልክ በመቀየር ረገድ ትልቅ ስኬት እያስገኘ ይገኛል።
ባለፉት አያሌ ዓመታት የኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ገፅታ በአብዛኛው ከድርቅ፣ ከረሃብና ከተረጂነት ጋር የተያያዘ ነበር። የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ግን ይህንን ታሪክ በመቀየር ረገድ የካርበን ዲፕሎማሲ መሣሪያ ሆኗል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ሰለባ ብቻ ሳትሆን፣ ለችግሩ ዓለም አቀፋዊ መፍትሔ የምታበረክት ግንባር ቀደም ሀገር መሆኗን በተግባር አሳይታለች።
ይህ መርሐ ግብር ሀገራችን በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላትን አቅም ከመጨመሩም በላይ፣ ስሟ በአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂነት እንዲነሳ አድርጓታል።
እስከዛሬ የዛፍ ተከላ የሚታሰበው በገጠር ተራራማና የተራቆቱ አካባቢዎች ላይ ብቻ ነበር። የአረንጓዴ ዐሻራ ልዩ ስኬት ግን ይህንን አስተሳሰብ ሰብሮ ወደ ከተሞች መግባቱ ነው። እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች በፓርኮች፣ በደንና በዕፅዋት እንዲሸፈኑ በማድረግ የከተማ ገፅታን ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል።
ይህ የአረንጓዴ መሠረተ ልማት ግንባታ የከተማ ነዋሪዎችን የአኗኗር ዘይቤ ከማሻሻሉም በላይ፣ አዳዲስ የኢኮ-ቱሪዝም መዳረሻዎችን በመፍጠር ዘመናዊ፣ ማራኪና ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ አድርጎታል።


የአረንጓዴ ዐሻራ ትልቁና እስከዛሬ ብዙ ያልተወራለት ስኬት በሕዝቡ ሥነ-ልቦና ላይ ያመጣው ለውጥ ነው።
በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በአጭር ጊዜ ውስጥ መትከልና መንከባከብ መቻል፣ በዜጎች ዘንድ እኛም መለወጥ እንችላለን የሚል የጋራ ብሔራዊ ኩራትና የተስፋ ስሜት ፈጥሯል።
ይህ ስኬት በተለይም በወጣቱ ትውልድ ዘንድ ለሀገር ግንባታ አዎንታዊ አመለካከት እንዲሰፍን በማድረግ፣ የኢትዮጵያን ገፅታ ከውስጣዊ ጥርጣሬና አለመረጋጋት ወደ ውስጣዊ ጥንካሬና የአንድነት ስሜት አሸጋግሮታል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ደንን ከመፍጠር ባለፈ የግብርናው ዘርፍ አካል መሆን መቻሉ ሌላው ለየት ያለ ስኬቱ ነው።
የተተከሉት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች የፍራፍሬ እንዲሁም የቡናና የቅመማ ቅመም ተክሎች በመሆናቸው፣ መርሐ ግብሩ በቀጥታ ከምግብ ዋስትና እና ከውጭ ምንዛሪ ግኝት ጋር ተሳስሯል።
ይህ አካሄድ ኢትዮጵያ የአየር ንብረትን እየጠበቀች የምጣኔ ሀብት ዕድገትን ማረጋገጥ የምትችልበትን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ሞዴል ለዓለም ያሳየችበት በመሆኑ፣ የሀገራችን የልማት ገፅታ ወደ ላቀ ደረጃ አሳድጎታል።
በሔዋን ጌታቸው