Search

አረንጓዴ ዐሻራ፦ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ትንሣኤ እና የሉዓላዊነት ማረጋገጫ

ረቡዕ ሰኔ 10, 2018 61

 

የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በቢሾፍቱ ከተማ ሲጀመር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ሰፊ ጭብጥ ያለው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት አረንጓዴ ዐሻራን ከችግኝ ተከላ ባለፈ፣ ከሀገር ሉዓላዊነት፣ ከትውልድ ተስፋ እና ከኢኮኖሚ አውታሮች ጋር በጥልቀት የሚያስተሳስር ነው።

"ተስፋን እንትከል" የሚለው የዘንድሮው መሪ ቃል የነገን ብሩህ ታሪክ ዛሬ መጻፍን የሚያመለክት ነው።

ተስፋን መትከል በድህነት ትታወቅ የነበረችውን የትናንቷን ኢትዮጵያ ትርክት በመቀልበስ፣ ልጆቿ ጠግበው የሚበሉባት እና ለዓለም ገበያ ምርቶቿን የምታቀርብ ሀገር የመገንባት ሕልም ትንሣኤ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ይህ ብሔራዊ ንቅናቄ የዚህ ዘመን ትውልድ የትብብር ማሳያ መድረክ ሆኗል። አባቶቻችን በዓድዋ ተባብረው የውጭ ጠላትን እንደመለሱ ሁሉ፣ የዛሬው ትውልድ ደግሞ በአረንጓዴ ዐሻራ ተባብሮ ለሀገር ሉዓላዊነት ስጋት የሆነውን የአፈር መሸርሸርን እና የተፈጥሮ ሀብት ብክነትን እየተከላከለ ይገኛል።

 

እስካሁን የተተከሉት 48 ቢሊዮን ችግኞች እና ወደ 65 ቢሊዮን ለማድረስ የተያዘው ግብ በዓለም ታሪክ ወደር የማይገኝለት የሕዝብ ንቅናቄ ውጤት ነው።

ይህ ትብብር በማንኛውም ማኅበራዊ ስብስቦች፣ በሠርግ እና በምረቃ በዓላት ላይ እንደ ባህል ሥር ሰዶ ሊቀጥል እንደሚገባም ጥሪ ቀርቧል።

የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ለምግብ ዋስትና እና ለሀገር ሉዓላዊነት ያለው ሚና የላቀ ነው። አፈርን ከስደት ስንታደግ፣ የሀገራችን ግብርናም አዲስ ገጽታ ይላበሳል።

 

ለምግብ ዋስትና የሚያደርገውን አስተዋፅኦ ለመጨመርም በኢትዮጵያ በስፋት የማይታወቁ እንደ ካካዎ እና ማካዴሚያ (Macadamia) ያሉ ከፍተኛ የገበያ ተፈላጊነት ያላቸው ችግኞች እየተባዙ ነው።

መርሐ ግብሩ እንደ ግብርና፣ ቱሪዝም፣ የኃይል ልማት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ላሉት የኢኮኖሚ ምሰሶዎቻችን ቀጥተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

የቡና ኤክስፖርት ገቢያችን 600 ሚሊዮን ወደ 3 ቢሊዮን ዶላር ያደገው አረንጓዴ ዐሻራ ላይ በተሠራ ሥራ ነው።

የተፈጥሮ ሚዛን በመጠበቁ ምክንያት የተመለሱ የዱር አራዊት እና አዕዋፍ የውጭ ጎብኚዎችን በመሳብ ለቱሪዝም ትልቅ አቅም መፍጠራቸው የአረንጓዴ ልማታችን ውጤት ማሳያ ነው።

በተጨማሪም አካባቢን በማከም የውኃ ክምችታችንን እያሻሻለ ያለው አረንጓዴ ዐሻራ፣ ለአምራች ኢንዱስትሪው የሚቀርበውን ኃይል በማሳደግ ረገድም የማይተካ አስተዋጽኦ አለው።

ይህ ስኬት ኢትዮጵያ በዓለም የአየር ንብረት መድረኮች አፍሪካን በመወከል ቀዳሚ ተምሳሌት እንድትሆን አስችሏታል።

አረንጓዴ ዐሻራን እንደባዮ-ኢኮኖሚ' ኢንቨስትመንት አድርገን ልንመለከተው እንችላለን። ችግኝ መትከል የተራቆተ አካባቢን አረንጓዴ ከማልበስ ባለፈ፣ ኢትዮጵያን የዓለም አቀፉ የካርቦን ንግድ ተካፋይ ሊያደርጋት የሚችል ትልቅ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን መሣሪያ ነው። ለዚህም ሀገራችን ተጨባጭ ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች።

ያደጉ ሀገራት የካርቦን ልቀታቸውን ለማካካስ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር በሚከፍሉበት በዚህ ዘመን፣ የምንተክላቸው ዛፎች ለኢትዮጵያ አዲስ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት አቅም ፈጣሪዎች ናቸው።

በመሆኑም ማኅበረሰቡ ችግኝ ሲተክል፣ የነገውን የሀገራችንን የውጭ ምንዛሬ ክምችት እያሳደገ መሆኑን መገንዘቡ ለንቅናቄው የበለጠ ትርጉም ይሰጠዋል።

 

በእነዚህ ጠቀሜታዎቹ ምክንያት አረንጓዴ ዐሻራ ዛፍ የመትከል ዘመቻ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ የሌሎችን ድጋፍ ሳትጠብቅ በራሷ ልጆች ጥረት ከድህነት እንድትወጣ የሚያስችል ጽኑ የተስፋ መሠረት ነው።

በለሚ ታደሰ