Search

ለሞት የተሰጡ የሚንጊ ሕፃናትን ከመታደግ በእውቀት እስከ ማነፅ

ማክሰኞ ጥቅምት 11, 2018 67

ላሌ ሉቡኮ በደቡብ ኦሞ አሪ ዞን ጂንካ ከተማ የኦሞ ቻይልድ አዳሪ ትምህርት ቤት መሥራች እና ባለቤትም ነው።

ከ12 ዓመታት በፊት ከሚንጊ ማኅበረሰብ አንሥቶ ያሳደጋቸው ሕፃናት 6ቱ የተሻለ ውጤት በማምጣት ወደ ከፍተኛ የትምህት ተቋማት በመግባታቸው ደስታ እንደተሰማው ይናገራል።

በሚንጊ ማኅበረሰብ የሚጣሉ ሕፃናትን አንሥቶ በማሳደግ የሚጀምረው የላሌ ሉቡኮ ሕይወት “የኦሞ ቻይልድ” የመጀመሪያ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት እስከ መመሥረት ደረሰ። በትምህርት ጥራት ላይ በመሥራቱ ለበርካቶች የራቀውን ውጤትንም ማቅረብ ችሏል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በ2017 ዓ.ም ከ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ውስጥ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ “ኦሞ ቻይልድ” በክልሉ 3ኛ ደረጃን መያዙን የሚናገረው ላሌ ይህን ተሞክሮ ለማስፋት ከመምህራን፣ ከወላጆች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን ይናገራል። 

ላሌ ከጥቂት ዓመታት በፊት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አሪ ዞን ጂንካ ከተማ ከሚንጊ ማኅበረሰብ የሚጣሉ ሕፃናትን አንሥቶ በአንድ ማዕከል በማሳደግ የማኅበረሰቡን አመለካከት መቀየር ችሏል።

ማዕከሉን ወደ ትምህርት ቤት አሳድጎ የሕፃናትን ሕይወት በዘላቂነት ለመታደግ ከዓመታት በፊት መጻፍ እና ማንበብ የሚችል ትውልድ ለመፍጠር ጉዞውን መጀመሩን ይገልጻል።

በአርብቶ አዳሩ አካበቢ የትምህርት ተደራሽነት እና ጥራት ላይ የሚስተዋለውን ክፍተት ለመሙላት ከአዳሪ ትምህርት ቤት የጀመረው ላሌ፣ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን 900 ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ መሆኑን ከኢቢሲ ዶትስትሪም ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል።

በክልሉ 6 የአዳሪ ትምህርት ቤቶች በወላይታ ሶዶ፣ በጌዴኦ ዞን ዲላ፣ በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ፣ በጎፋ እና ኮሪ ዞኖች መኖራቸውን የገለጹት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ፀሐይ ወራሳ፣ በትምህርት ጥራት ላይ የራሳቸውን ሚና እየተወጡ ነው ብለዋል።

በክልሉ አርብቶ አደሮች አካባቢ የትምህርት ተደራሽነትን እና ጥራትን ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት እየሠሩ መሆኑን ጠቁመው፣ በግል የመደበኛም ሆነ የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን ከፍተው የሚያስተምሩ ግለሰቦች እና ተቋማት  የበኩላቸውን ድርሻ እያበረከቱ ነው ብለዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአሪ ዞን አርብቶ አደሩ ጋር ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በተሠረው ሥራ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ  ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ሳቢ እና ምቹ ካባቢን በመፍጠር፣ ተጨማሪ ክፍሎችን በመገንባት፣ ለመምህራን ሥልጠና በመስጠት፣ የአቅም ችግር ያለባቸውን ልጆች በቁሳቁስ የመደገፍ ሥራዎች መሥራታቸውን ተናግረዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በትምህርት ዘመኑ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ተመዝገበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ መሆናቸውን ከክልሉ ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመልክታል።

በመሀመድ ፊጣሞ

#EBC #ebcdostream #education #mingi