የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “መስጠት አያጎድልም፣ በጎ ፈቃደኝነት ለሀገር ማንሰራራት” በሚል የእውቅና መርሐ-ግብር በማካሄድ በ2017 ዓ.ም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ልበ ቀናዎችን አመስግኗል።
ይህን በተመለከተ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት፥ በዚህ ሰው ተኮር በሆነው እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አርያነት ተጀምሮ በመላው ነዋሪዎቻችን ዘንድ የየዕለት ተግባር እና ባህል በሆነው የበጎነት ሥራ በርካታ ውጤቶች ተገኝተውበታል ብለዋል።
አክለውም፥ የፈሰሱ ዕምባዎች ታብሰዋል፤ ያዘመሙ ቤቶች ተቃንተዋል፤ የአገር ባለውለታዎች፣ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው፣ ለከፋ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር የተጋለጡ በርካታ ወገኖቻችንን በመርዳት የኑሮ ጫናቸው እንዲቃለል ተደርጓል ነው ያሉት።

አዲስ አበባ ባለፉት 7 የለውጥ ዓመታት ወጣቶቿን፣ ባለሀብቶቿን፣ መላው ነዋሪዎቿን፣ የተለያዩ የሙያ ዘርፍ ባለቤቶችን አስተባብራ ዓመቱን ሙሉ በዘለቀ የበጎ ፈቃድ ተግባር ውስጥ በማሳተፍ እና ከ42 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት በበጎ ፈቃድ ተግባር በማሰባሰብ የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት ተችሏል ብለዋል።
በ2017 ዓ.ም ብቻም ከ16 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ ለተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች እንዲውል ተደርጓል ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ከዚህ ውስጥ 2.2 ቢሊዮን የሚሆነውን በማበርከት የዘንድሮውንም ልዩ ሽልማት የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ መውሰዱን አስታውቀዋል።
በዚህ በምድርም በሰማይም ዋጋው ከፍ ባለ መልካም ተግባር ውስጥ በተለያየ መንገድ ያለ ስስት አሻራቸውን ላኖሩ፣ መስጠት ላላጎደለባቸው ልበ ቀና የከተማዋ ነዋሪዎች በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።
ነዋሪዎቹ ይህን ትውልድ ተሻጋሪ አኩሪ የበጎነት ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉም ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል።
#ebcdotstream #addisababa #communityservice #socialresponsibility