ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት ከአንድም ሁለት ሦስት ወደቦችን ታስተዳድር የነበረች ሀገር ነች፡፡
የአክሱም መንግሥት በዓለም ላይ ከሚገኙ አራቱ ኃያላን መካከል አንዱ በነበረበት ወቅት አዱሊስ በጣም አስፈላጊው እና የኢኮኖሚው ምሕዋር ነበር።
ከ1ኛው እስከ 9ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኃያል የነበረው የአክሱም መንግሥት የኃያልቱ ሚስጢር በቀይ ባሕር ላይ የንግድ መሥመርን መቆጣጠሩ እንደነበር የThe Axumite Kingdom Trading Empire Located in Modern-day Ethiopia and Eritrea - 872 Words | Bartleby ጥናት በግልጽ አስቀምጦታል።
ኢትዮጵያን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የባለሙያዎችን ጥናቶች የሚያቀርበው የኢትዮጵያ ስትራቴጂክ ጥናት ተቋም፤ አውሮፓውያን አፍሪካን በቅኝ ግዛት ከመቀራመታቸው በፊት ኢትዮጵያ በአዱሊስ እና ምፅዋ በኩል አድርጋ በቀይ ባሕር ላይ ከዓለም ጋር ትገናኝ እንደነበር ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትን ይጠቅሳል፡፡
እነዚህ ጥንታዊ የንግድ መስመሮች ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን ተጠቅማ በቀጣናው ያላትን ታሪካዊ ሥልጣኔ እንድትኖር ያስቻሏት ናቸው።
ኢትዮጵያን ስልታዊ በሆነ መንገድ ከቀይ ባሕር የመነጠል ሴራ መጠንሰስ የተጀመረው ከአውሮፓ ኃይል በአካባቢው መስፋፋት ጋር ተያይዞ ነበር፡፡
በዚህ ውስጥ ግብፅን እና ሱዳንን ስትገዛ የነበረችው እንግሊዝ ዋናዋ ተዋናይ እንደነበረች ታሪክ ዋቢ ነው፡፡ በሴራው ጥልፍልፍ ምፅዋን የያዘችው ጣሊያን አሰብን ሩባቲኖ በተባለ ኩባንያ በኩል በመግዛት የቅኝ ግዛቷ አካል አደረገችው፡፡
ኤርትራ ከጣሊያን ቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር በኮንፌዴሬሽን ስትዋሃድ ኢትዮጵያ መልሳ የባሕር በር እና የጠንካራ ባሕር ኃይል ባለቤት ሆና ቆይታለች::
በቅኝ ግዛት ወቅት ተወሳስቦ የነበረው የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር መዳረሻ ጥያቄ በ1985 ዓ.ም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትለይ እንደገና ሌላ ፈተና ውስጥ ገባ፡፡ የወቅቱ የኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት ለኤርትራ የሀገርነት ዕውቅና ሲሰጥ ራስ ገዝ የነበረችውን አሰብንም ጠቅልሎ አስረከበ፡፡
ኢትዮጵያ ወደብ እንድታጣ የተደረገው በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እና በወቅቱ ሥልጣን ይዞ በነበረው ኃይል አሻጥር እንደነበር በወቅቱ ጉዳዩን ይከታተሉ የነበሩ ወገኖች ግልጽ አድርገውታል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የነበሩት ግብፃዊው ቡቱሩስ ቡቱሩስ ጋሊ የድራማ ዋና ደራሲነት እና በኢትዮጵያ መሪዎች ተዋናይነት ሁለት የባሕር በር የነበራት ኢትዮጵያ በአንድ ጀነበር ባዶ እጇን ቀረች፡፡
ደርግ ከሥልጣን ሲወርድ በካርተር ማዕከል በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ የነበሩት ጂሚ ካርተር የወቅቱን ሁኔታ፣ "በ1991 ኢሕአዴግ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጣን ሲይዝ ስለ ኤርትራ ጉዳይ ስጋት ነበረኝ፣ ነገር ግን ኢሕአዴግ በ1993 ለኤርትራ ሙሉ ነፃነቷን በመስጠት እና ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር በማቋራረጥ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ይዛ ወደብ አልባ ሀገር እንድትሆን አድርጓታል" በማለት ጽፈዋል።
በ1997 ዓ.ም ምርጫ የቅንጅት አመራር የነበሩት ፕሮፌሰር ያዕቆብ ኃይለማርያም የባሕር በር ጉዳይን ከፍ አድርገው ያነሱ ምሁር ናቸው፡፡ "አሰብ የማን ናት?" በሚለው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታጣ የተደረገችበትን ሁኔታ እና መልሳ ልታገኝ የምትችልበትን ሕጋዊ መንገድ በግልጽ አስቀምጠዋል፡፡
ይህ ግፍ የተሠራባት ኢትዮጵያ ከዚያ በኋላ ስለ ባሕር በር ጉዳይ የሚጠይቁ ዜጎች የሌላውን ሀገር ሉዓላዊነት እንደጣሱ ተደርጎ በመንግሥት ሲከሰሱ ቆይተዋል፡፡
ከመጀመሪያው እስከ ሥድስተኛው ምርጫ ድረስ በምርጫ ክርክራቸው የባሕር በር ጥያቄን የመወዳደሪያ ነጥባቸው አድርገው የተንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁሉ በኢሕአዴግ "የደርግ ሥርዓት ናፋቂ" ተደርገው ተፈርጀዋል፡፡
በ2010 ዓ.ም የመጣው የለውጥ ኃይል ወደ ፊት ካመጣቸው ጉዳዮች አንዱ የኢትዮጵያ ዋና ስብራት በሆነው የባሕር በር ጉዳይ ነው፡፡
የባሕር በር መልሶ መቋቋም፣ ከኤርትራ ጋር የነበሩ ንግግሮች እና ሌሎች አጋሮችን በማስተባበር በዚህ ዘርፍ ድጋፍ እንዲያደርጉ ማድረግ በመንግሥት የተወሰዱ የመጀመሪያዎቹ ወሳኝ እርምጃዎች ነበሩ፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ደግሞ የባሕር በር ጥያቄ የኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ እና የትውልድ ጥያቄ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አደባባይ አውጥተውታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመድ ጥናትን ጠቅሰው እንደገለጹት፤ የባሕር በር ተደራሽነት ከአንድ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) እስከ 25-30 በመቶ ይሸፍናል፡፡ ይህም የሕዝብ ቁጥሯ በፍጥነት እያደገ ያለውን እና የቀጣናው አስተሳሳሪ ለሆነችው ኢትዮጵያ ቀይ ባሕር የህልውናዋ ጉዳይ እንደሆነ ማሳያ ነው።
የቀይ ባሕርን በጋራ መጠቀም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምን፣ አንድነትን እና ብልጽግናን እውን ሊያደርግ እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፅንዖት ሲገልጹ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በርን የምትጠይቀው በሰላማዊ መንገድ እና በሰጥቶ መቀበል መርሕ መሆኑንም ደጋግመው ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህም ለየኢትዮጵያ አየር መንገድን፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እና ኢትዮ-ቴሌኮምን ጨምሮ ድርሻ እስከ መስጠት ደረስ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
ይህ አካሄድ ከዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ እና ትብብር መርሆዎች ጋር የሚስማማ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ገንቢ በሆነ ውይይት ያላትን ፍላጎት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በግልጽ አስታውቃለች።
ይህ ዓለም አቀፍ ሕግን የተከተለው የኢትዮጵያ ጥያቄ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ቢታመንበትም ወደ መፍትሔ ለመሄድ ግን ዳተኝነቱ ቀጥሏል፡፡
ነገር ግን የባሕር በር ተዘግቶባት 30 ዓመታትን ለመቆየት የተገደደችው ኢትዮጵያ ደግሞ ጥያቄዋ ምላሽ እንዲያገኝ ሌላ 30 ዓመት መጠበቅ እንደማትችል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር በር ተዘግቶባት የመጨረሻው በደል የተፈፀመባት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የባሕር በር ማቋቋም ያስፈለገውም ኢትዮጵያን ከዚህ እስር ለማላቀቅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የአሰብን ጉዳይ አስመልክቶ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ብዙ ርቀት ሄዳ የአሰብን መንገድ ጥገና እስከ መጀመር ተደርሶ ጉዳዩ በኤርትራ ወገን ወደ ኋላ እንደተመለሰ ግልጽ አድርገዋል፡፡
አሰብ ላይ ሕይወት ለመዝራት የተጀመረው እንቅስቃሴ በዚሁ በኤርትራ መንግሥት እምቢተኝነት መክሸፉን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ለዘላለም ተዘግታ እንደማትኖር ነገር ግን አሁንም ለሰላም ቅድሚያ እንደምትሰጥ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የቀይ ባሕር ጥያቄ የታሪክ፣ የመልክዓ ምድር፣ ከሁሉም በላይ የትውልድ ጥያቄ ስለሆነ ከዚህ በኋላ የሚቀለበስ አይደለም ብለዋል፡፡ እናም የሚያዋጣው ለሁሉም የሚበቃውን፣ ሌሎች ጭምር ባሕር አቋርጠው የሰፈሩበትን ሀብት በጋራ ተጠቅሞ በጋራ ማደግ የኢትዮጵያ አቋም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በለሚ ታደሰ