Search

የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ የተመድ ኮንቬንሽንን ያማከለ ነው

ቅዳሜ ጥቅምት 22, 2018 106

ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ የሥልጣኔ እና የንግድ ማዕከል በመሆን በሺህ ለሚቆጠሩ ዘመናት መዝለቁን የታሪክ ፀሐፊዎች እና ተመራማሪዎች ምስክር ናቸው።
የአሁኑ የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ኮንቬንሽንን ያማከለ ስለመሆኑም ምሁራን ይገልጻሉ።
የፖለቲካ ሳይንስ እና ፍልስፍና ምሁሩ ሰለሞን አሊ (ዶ/ር) ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ወሰን የመሆኑ ታሪክ የደበዘዘ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በ1983ቱ የመንግሥት ለውጥ ማግስት በወቅቱ ሀገሪቱን ያስተዳድር በነበረው አካል ግልፅነት በጎደለው መንገድ ለሌላ አካል ተላልፎ መሰጠቱን አንስተዋል።
በወቅቱ በኢትዮጵያ ላይ ይህን ሴራ የፈፀሙ አካላትን የተቃወሙ እና የሞገቱ እንደነበሩም አስታውሰዋል።
በዚህ ሴራ ለዘመናት ከደመቀችበት የቀይ ባሕር ቀጣና ለ3 አስርት ዓመታት ተገልላ መቆየቷ አግባብ አይደለም ብለዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሀገሪቱ እና ዜጎቿ ከተፈጥሮ ወሰናቸው በመገለላቸው የኢኮኖሚ ጥገኝነት እና የደህንነት ስጋት እንዲጋረጥባቸው ሆኗል ሲሉ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ላይ የተሴረው ሴራ በዓለም አቀፍ ሕግ ፊት አግባብነት እና ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑ ባሻገር የተሰራውን ስህተት ለማረም የሰጥቶ መቀበል ዲፕሎማሲ አማራጭም ስለመኖሩ ተናግረዋል።
አሁን ላይ ያለው መንግሥት እና የዜጎች የባሕር በር ይገባኛል እሳቤ እና ጥያቄ ሕጋዊ እና አግባብነት ያለው ስለመሆኑም አክለዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ የሀገሪቱን መጻኢ ዕድል የሚወስን እንደሆነም በአጽንኦት ተናግረዋል።
በዲላ ዩንቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ዳዊት መዝገበ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ አሁን እያነሳችው ያለው የባሕር በር ጥያቄ ከተመለሰ፤ ጉልህ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር መሻቷን ለማሳካትም ለሰላማዊ ንግግር ቅድሚያ እንደምትሰጥ ተናግረዋል።
በሜሮን ንብረት