በዓለም ላይ 44 የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት አሉ። ኢትዮጵያ በተፈፀመባት ሴራ አማካኝነት የባሕር በር ከአጣች 3 አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል። ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄን በሰላማዊ መንገድ መጠየቅ ከጀመረችም ሰነባብታለች።
ፍትሐዊውን ጥያቄም በርካታ ሀገራት እየተረዱት መጥተዋል። የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት አሊ ሁሴን (ዶ/ር) ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ቀደም ባለው ታሪክ የባሕር በር ኖሯት በኋላም በግፍ የተነጠቀች በመሆኗ ሁኔታው ከተቀሩት 43 የባሕር በር አልባ ሀገራት ጋር ሲታይ የተለየ ታሪክ እንዳለው አስረድተዋል።
የባሕር በር የቀጣናውን ሰላም ለማስጠበቅ እና የተሻሉ ሥራዎችን ለመሥራት እንደሚያግዝ ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ከሸቀጣ ሸቀጥ ዝውውር ባሻገር የቀጣናዊ ውህደትን ያለመና ፋይዳውም የጎላ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አምባሳደር ተውፊቅ አብዱላሂ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የትውልድ ቁጭት ነው ይላሉ።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን ለማሳካት በሰላማዊ መንገድ እየሰራች እንደሆነም አንስተዋል። ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ መፍትሔ እስከሚያገኝ ድረስ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ወዳጆች ከመሻት ባለፈ የተጠናከረ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውም አንስተዋል።
በሜሮን ንብረት
#EBC #ebcdotstream #redsea