Search

የቦታ እጥረት ያላገደው የሲንጋፖር የሕንፃ ላይ የዓሣ እርባታ

ቅዳሜ ጥቅምት 22, 2018 49

በሲንጋፖር ለሰዎች መኖሪያ ወይም ለቢሮ ሳይሆን ለተለየ ልማት ተብሎ የተገነባ ግዙፍ ሕንፃ ይገኛል።
ይህ ሕንፃ በ65 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ለዓሣ እርባታ ተብሎ የተገነባ ከመሬት በላይ ባለ ስምንት ወለል ሕንጻ ነው።
ዛሬ ላይ በዓለማችን ካሉት የበለፀጉ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሲንጋፖር፣ እዚህ ደረጃ ከመድረሷ በፊት አስከፊ የሚባሉ የድህነት ታሪኮችን አሳልፋለች።
ይህ ታሪክ ከመቀየሩ ከጥቂት አስርት ዓመታት በፊት የዜጎቿ የነፍስ ወከፍ ገቢም እጅግ ዝቅተኛ ነበር። በሌላም በኩል ውስን የሆነው መሬቷ ብዙ ሕዝቧን ለመመገብ አስቸጋሪ በመሆኑ በምግብ እጥረት ትፈተን ነበር።
በእነዚህና መሰል ችግሮች በድህነት አዘቅት ውስጥ የነበረችው ሀገር አዲስ ታሪክ ለመፃፍ ተነሳች።
 
የዘመናዊቷ ሲንጋፖር መስራች አባት ተብለው በሚታወቁት በጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኩዋን ዩ አማካኝነት በተቀረፀ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካኝነት የድህነት ታሪኳን ሰርዛ ሕዝቧን የሚያኮራ የአዲስ ታሪክ ባለቤት ለመሆን በሙሉ ልብና ተነሳሽነት መጓዝ ጀመረች።
ከ6 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚኖርባትና በስፋቷ በአማካይ አዲስ አበባን የምታክለው ሲንጋፖር፣ ከ90 በመቶ በላይ ለምግብ ፍጆታነት የሚውሉ ምርቶችን ከውጭ ሀገራት ታስመጣ ነበር።
የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ያላት የቆዳ ስፋት እጅግ ያነሰ በመሆኑ ከመኖሪያና ለኢንዱስትሪ ከተከለሉ ቦታዎች ተርፎ ለእርሻ አገልግሎት የሚውል መሬት ባለመኖሩ ነው።
በዚህ ምክንያት በሲንጋፖር ለእርሻ የሚውለው የመሬት ስፋት ከጠቅላላ ሀገሪቱ ከአንድ በመቶ በታች ነው።
 
ሆኖም ከቅርብ ጊዜ በኋላ ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ያለመችው ሲንጋፖር '30... 30' የሚል ስያሜ ያለው እቅድ ቀርጻ ያንን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እያደረገች ነው።
ይህ እቅድ እ.አ.አ. በ2030፣ ቢያንስ ሰላሳ በመቶ የሚሆነውን አጠቃላይ የምግብ ፍጆታዋን በሀገር ውስጥ ለማምረት እንዲሁም ከአንድ በመቶ በታች በሆነው ለግብርና የሚሆን መሬት ላይ ፕሮጀክቶቿን ለመተግበር የሚያስችል ሥራን የያዘ ነው።
በዚህም መሰረት ሲንጋፖር የግብርና ሥራዋን ለማዘመን የሚረዳ የማማ ላይ እርሻዎችን መጠቀም የጀመረች ሲሆን፣ በጥቂት ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ብዙ ምርት ለማግኘት በሚያስችለው በዚህ የከፍታ ግብርና ሥራ ውጤታማ መሆን ችላለች።
‘ስካይ ግሪንስ’ በተባለውና በተመሳሳይ ኩባንያዎች አማካኝነት መልማት የጀመረው ይህ የእርሻ ሥርዓት አትክልቶች የሚዘሩት በመሬት ላይ ሳይሆን እስከ 9 ሜትር ቁመት ባላቸው ቀጥ ያሉ የአሉሚኒየም መደርደሪያዎች ላይ ነው።
በተጨማሪም ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ዓሣዎችን ማርባት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ተነድፈው ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል ከጥቂት ዓመታት በፊት የተገነባው የአፖሎ አኳካልቸር ዓሣ እርባታ ይገኝበታል።
በዚህ በአይነቱ አዲስ የሆነው የዓሳ እርባታ ስምንት ፎቅ ያለውና በውስጡም በእያንዳንዱ ሕንጻ ላይ በተለያየ መጠን የተገነቡ ትላልቅ ገንዳዎች ያሉት ነው። በኮምፒውተር የታገዘ የውኃና የኦክስጅን ቁጥጥር ለማድረግ የሚረዱ ዘመናዊ መሣሪያዎችም ተገጥመውለታል።
የቦታ ውሱንነት ከመልማት ያላገዳት ይህች ሀገር የሕዝቧን የምግብ ፍላጎት ለመሸፈን ይህን መሰል ዘዴዎችን በመጠቀም ለሌሎች ሀገራት ምሳሌም እየሆነች ትገኛለች።
እዚህ ደረጃ ከመድረሷ በፊት አስከፊ የሚባሉ የድህነት ታሪኮችን ያሳለፈችው ሲንጋፖር፣ ዛሬ ላይ በዓለማችን ጠንካራ ኢኮኖሚ ካላቸው ሃብታም ሀገራት መሀከል አንዷ ናት።
 
በዋሲሁን ተስፋዬ