በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ፍላጎት ሳይኖር በአንድ የፖለቲካ ቡድን ውሳኔ ብቻ የባሕር በርን ያህል ለዘርፈ-ብዙ ዕድገት ወሳኝ አበርክቶ ያለው ሐብት መነፈግ አንገብጋቢ ነው ሲሉ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን እና ተመራማሪ አበበ አኖ (ዶ/ር) ገለጹ።
ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታገኝ የሚደረገው ጥረት መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ የባሕር በር ከነበራቸው ቀደምት ሀገራት መካከል እንደነበረች አውስተዋል።
በነበራት የባሕር በርም ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ጋር በንግድ፣ በጉብኝት እንዲሁም በሌሎች ሥራዎች ጥብቅ ቁርኝት እንደነበራት አስታውሰው፤ ይህንም ታሪክ እንደሚመሠክርም አስረድተዋል።
ነገር ግን ከዚህ ቀደም በነበረው የፖለቲካ ሁኔታ በተፈጸመ ታሪካዊ ስህተት የነበራትን ባሕር በር እንድታጣ መደረጉ አስቆጭም፤ አሳዛኝም መሆኑን ተናግረዋል።
በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ፍላጎት ሳይኖር በአንድ የፖለቲካ ቡድን ውሳኔ ብቻ የባሕር በርን ያህል ለዘርፈ-ብዙ ዕድገት ወሳኝ አበርክቶ ያለው ሐብት መነፈግ አንገብጋቢ ነው ብለዋል።
ተጨማሪ ቁጭት የሚፈጥረው ደግሞ ከለውጡ በፊት ለበርካታ ዓመታት የባሕር በር ጥያቄው በመንግሥት ደረጃ ‘ጆሮ ዳባ’ መባሉ ነው ይላሉ።
የሆነው ሆኖ የባሕር በሯ የተወሰደበትም ሆነ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም የተባለበት ሁኔታ ቢያስቆጭም፤ በለውጡ መንግስት ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት እንዳለባት ታምኖ አሁን ጥረቶች መጀመራቸው ተገቢ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ የነበራትን ተቀምታ፣ ከቀይ ባሕር በቅርብ ርቀት ላይ ሆና፣ የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ሆና እና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ይዛ የበይ ተመልካች ልትሆን እንደማይገባ አብራርተዋል።
ስለሆነም የራሷን ግዛት አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ያጣች ሀገር መሆኗን የሀገራት መሪዎች እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተገንዝቦ እንዲያግዝ ሁላችንም የሚጠበቅብንን መወጣት ይገባናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብም የባሕር በር ለበለጸገች ሀገር አስፈላጊ መሆኑን ተረድቶ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መዋጣት እንዳለበትም አመላክተዋል።
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #seaaccess