በዓለማችን የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ሀገራዊ ምክክርን ለማካሄድ ሲወጥኑ የተለያዩ ውስጣዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት እንደሆነ እሙን ነው፡፡
ሂደቱ ላለመግባባት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት ባለድርሻ አካላት ምክክር እንዲያደርጉ በመጋበዝ ሀገራዊ መግባባት እና ሰላም እንዲሰፍን አበክሮ ይሰራል፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ ሀገራዊ ምክክርን ለማካሄድ አመቺ ጊዜ እና ዓውድ መፈጠር እንዳለበት ተሞክሮዎች ያመለክታሉ፡፡ የኢትዮጵያን ተሞክሮ ጨምሮ በአንዳንድ ሀገራት እንደሚስተዋለው ሂደቱ ከግጭት በፊት፣ በግጭት ዓውድ ውስጥ እንዲሁም ከግጭት በኋላ ሲካሄድ መመልከት ተችሏል፡፡
ለመሆኑ በእነዚህ ሦስት ዓውዶች ውስጥ የሚካሄዱ የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ዓላማቸው ምንድነው? ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮስ ምን ይመስላል?
ይህ ዓውድ በባለድርሻ አካላት መካከል ያሉ ውጥረቶች፣ የፖለቲካ ትኩሳቶች እንዲሁም ስልጣንን እና ሀብትን ለመያዝ የሚደረጉ ጤናማ ያልሆኑ ፉክክሮች የሚስተዋሉበት ነው፡፡ በዚህ ዓውድ ውስጥ የሚከናወን የሀገራዊ ምክክር ሂደት እነዚህን ውጥረቶች በማርገብ በባለድርሻ አካላት መካከል መተማመን ለመፍጠር ይሰራል፡፡
ለዚህም እንደ ዓይነተኛ ምሳሌ የሚጠቀሰው እ.አ.አ በ2013 የተካሄደው የቱኒዚያ የሀገራዊ ምክክር ሂደት ሲሆን በገዥው ፓርቲ እና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የነበረውን የሃሳብ ልዩነት ተከትሎ ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ተገድለዋል፡፡ ይህም በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ ውጥረት እና አመፅ በማስከተሉ ሁኔታውን ለማብረድ አራት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በጋራ ሆነው የሀገሪቱን የምክክር ሂደት እንዲመሩ መንስኤ ሆኗል፡፡
ያንን ተከትሎ ባለድርሻ አካላት ከግጭት የፀዳ የፖለቲካ ስምምነት በማድረግ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት በሀገሪቱ ውስጥ መፍጠር ችለዋል፡፡
ይህ ዓውድ የተፋፋመ የተፋላሚ ኃይሎች ጦርነት የሚካሄድበት ነው፡፡ ይህም በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ሕይወት በመቅጠፍ ለንብረት መውደምና መፈናቀል ከመዳረጉም በላይ እነዚህ ኃይሎች በፖለቲካ ቅርቃር ውስጥ የሚገቡበት ወቅት ነው፡፡
በዚህ ጊዜ ውስጥ የሚከናወኑ የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ሰላምን ለማስፈን ዒላማ የሚያደርጉ እንደመሆናቸው መጠን የዚህ ዓውድ ባህሪ ተፋላሚ ወገኖች ለንግግር ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ መጋበዝ እና መወትወት ነው፡፡ ይህም ተፋላሚ ሃይሎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሂደቱ ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ ዘላቂ ለሆነ የፖለቲካ መፍትሄ የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ በር ከፋች ነው፡፡
ለዚህም በምሳሌነት የሚጠቀሰው እ.አ.አ በ2013 የተደረገው የየመን ሀገራዊ ምክክር ነው፡፡ በዓረብ አብዮት ምክንያት አለመረጋጋት ውስጥ ቆይታ የነበረችው የመን፣ በገልፍ ኮርፖሬሽን ምክር ቤት አማካኝነት የተለያዩ የሀገሪቱ ባለድርሻ አካላት በሀገራቸው ጉዳይ ምክክር እንዲያደርጉ መደላድል ፈጥራለች፡፡ በተፈጠረው መደላድል ተፋላሚዎች ተኩስ አቁም ስምምነት አድርገው ቁጭ ብለው በጠረጴዛ ዙሪያ ለመነጋገር እና እርስ በእርስ ለመደማመጥ ፈቃደኝነታቸውን ያሳዩበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡
በግጭት ማግስት ያሉ ሀገራት የተለያዩ መገለጫዎች ያሏቸው ቢሆንም በዋነኝነት በተፋላሚ ኃይሎች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት የሚደረግበት እና የአገዛዝ ለውጥ ለማድረግ ስምምነት ላይ የሚደረስበት ነው፡፡ በግጭቱ ወቅት የተፈጠሩ የሕይወት መጥፋቶች፣ የንብረት መውደሞች እንዲሁም መፈናቀሎች የፈጠሯቸው ቁርሾዎች መለዘብ ስለሚገባቸው ሂደቱ በዋነኝነት ዕርቅን ለማስፈን እና የሀገር ግንባታ ሂደትን ስኬታማ ለማድረግ ዒላማ በማድረግ የሚካሄድ ነው፡፡
በ2003 ተጀምሮ በ2005 የተጠናቀቀው የላይቤሪያ የድህረ-ጦርነት ሀገራዊ ምክክር ለዚህ ዋነኛ ማሳያ ነው፡፡ ሀገሪቱ ለረዥም ዓመታት ከቆየችበት ደም አፋሳሽ ጦርነት በመውጣት ሁለት ዓመት የቆየውን የምክክር ሂደት በማድረግ ሰላማዊ የሆነ የምርጫ ሂደት ማካሄድ ችላለች፡፡ ይህም ለሀገሪቱ ሰላም ወሳኝ ሚና ተጫውቷል፤ ትልቅ መሰረትንም ጥሏል፡፡
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ተቋቁሞ ወደ ስራ ሲገባ በኢትዮጵያ በሚገኙ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነት እና አለመግባባት የሚታይ መሆኑን መነሻ አድርጎ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከላይ በተዘረዘሩት የግጭት ዓውዶች እያለፈች መሆኑን ይገነዘባል ያለው ኮሚሽኑ፤ በእስካሁኑ ሂደት ከእነዚህ የግጭት እና የፖለቲካ ውጥንቅጥ አዙሪቶች ለመውጣት በሚደረገው ጥረት የበርካታ ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ስላልተለየው ምስጋና አቅርቧል፡፡
በተለይም በዚህ ወቅት በግጭት እና በድህረ-ግጭት ውስጥ የሚገኙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የዚህ ሂደት ተሳታፊዎች እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲደረግለት ኮሚሽኑ በድጋሚ ጥሪ አቅርቧል፡፡