ኢትዮጵያ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩ የታሪክ፣ የሕግ እንዲሁም ከተለያዩ ዘርፎች የተሰባሰቡ ምሁራን እንደሚያስፈልጓት ከኢቲቪ ዳጉ ፕሮግራም ጋር ቆይታ ያደረጉ እንግዶች ገልጸዋል፡፡
ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት የባሕር በር የነበራት ኢትዮጵያ፣ የባሕር በር ጥያቄዋ ግዛትን የማስፋፋት ጉዳይ ሳይሆን ብሔራዊ ሕልውናዋን የማረጋገጥ ነው ሲሉ የቀድሞ ባሕር ኃይል አባል ሌፍተናንት ፈረደ አየለ ተናግረዋል።
የነበረንን የባሕር በር ያጣነው ተገቢ ሥልጣን ባለው አካል እስካልሆነ እና በሕገ መንግሥት እስካልተደገፈ ድረስ ተቀባይነት የለውም ነው ያሉት የቀድሞው ባሕር ኃይል አባል።
ኢትዮጵያ ዳግም የባሕር በር እንዲኖራት ታሪኮችንና ሕጋዊ መርሆችን በማገናዘብ የሀገሪቱን ጥቅም የሚያስከብር የምሁራን ስብስብ ያስፈልጋል ብለዋል ።
የሺፒንግና ወደብ አስተዳደር ባለሙያ የሖኑት አህመድ ያሲን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የባሕር መብት እና ግዴታ የሚጠየቅበትን ሰነድ ካዘጋጁት ሀገራት መካከል መሆኗን አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት በዓለምአቀፍ ደረጃ በሰነዶች የተደገፈ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡
ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ የሀገሪቱን ጥቅም የሚያስከብሩ ምሁራን ያስፈልጋሉ ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የነበራትን የባሕር በር ያጣችው ተጨባጭ ባልሆነ ምክንያት እና ተገቢነት በሌለው አካል ነው ያሉት ደግሞ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ፖለቲካ ተመራማሪ አሊ ሁሴን (ዶ/ር) ናቸው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ኮንቬንሽንን መነሻ በማድረግ ኢትዮጵያ አሁን የጀመረችውን ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ መግፋት ይኖርባታል ነው ያሉት።
በቢታንያ ሲሳይ