Search

በአርሲ ዞን የተከሰተውን ችግር እንዲያጣራ የተሰየመው የአጣሪ ኮሚቴ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን ይፋ አደረገ

ሰኞ ኅዳር 01, 2018 214

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በኦሮሚያ ክልል፣ አርሲ ዞን በጉና፣ በመርቲ፣ በሸርካ እና በሆሎንቆ ዋቢ ወረዳዎች የተፈጠረውን ችግር እንዲያጣራ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ ተወካዮችን ያካተተ ግብረ ኃይል አቋቁሞ ችግር ወደ ተከሰተባቸው ወረዳዎች አሰማርቷል።
አጣሪ ኮሚቴው ችግር ወደ ተከሰተባቸው አራት የአርሲ ዞን ወረዳዎች በአካል በመሄድ ጉዳዩን ለአምስት ተከታታይ ቀናት ሲያጣራ ቆይቶ በአጣሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ እና ም/ሰብሳቢ የመጀመርያ ደረጃ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል፡፡
አጣሪ ኮሚቴው በእነዚህ ወረዳዎች የሰዎች መገደል፣ መታጋት እና የንብረት ውድመት መከሰቱን ከአካባቢው ማህበረሰብ እና ጉዳት ከደረሰባቸው ወገኖች መረጃ ማግኘቱን አሳውቋል፡፡
የተገደሉት ሰዎች እንዲሁም የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት ያጋጠማቸው ዜጎች የአንድ የሃይማኖት ተከታይ እና አገልጋዮች አለመሆናቸውን፤ ሃይማኖት እና ዘር ሳይለይ ግድያና ጥቃት እንደተፈጸመ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
ይህን ወንጀል የፈጸሙት አካላትም ራሳቸውን በተለያየ ስም የሚጠሩ እና የመንግሥት የጸጥታ ኃይል ችግር ወደ ተከሰተባቸው ስፍራዎች ሲንቀሳቀስ ስፍራዎቹን በፍጥነት በመልቀቅ በጫካ የሚደበቁ የታጠቁ ኃይሎች መሆናቸውን ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው የአካባቢው ማህበረሰቦች ኮሚቴው መረዳት መቻሉን አሳውቋል፡፡
የኮሚቴው ሰብሳቢ መላዕከ ሰላም ዳዊት ያሬድ ችግሩ ተጋላጭ የአንድ ወገን ብቻ ያነጣጠረ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ሐጅ አብዱልሀኪም ሁሴን ችግሩ ብሄር ወይም ሃይማኖት መሰረት ያደረገ አለመሆኑን ነው የገለጹት፡፡