Search

በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ሥራ ተስፋ ሰጪ የተባለው አዲሱ የቻይና ግብ

ሰኞ ኅዳር 01, 2018 4242

30ኛው የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP30) እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከገባችበት ፈተና እንድትወጣ ከጊዜ ጋር የፈጠነ ውሳኔ እንደሚያስፈልግ በርካቶች እያሳሰቡ ነው።

በዚህ ወሳኝ ወቅት ቻይና ያስተዋወቀችው የ2035 ሀገር አቀፍ ቃል ኪዳን (NDCs) የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም አስደናቂ እና ተስፋ ሰጪ ጅምር ነው ተብሏል።

የቻይና የ2035 ቃል ኪዳን ለሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ጂኦፖለቲካዊ እና አካባቢያዊ ገጽታን የሚቀይር ትልቅ ቁርጠኝነትን ያሳየ ነው በሚልም ተወድሷል።

ቻይና እ.አ.አ. እስከ 2035 የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀትን አሁን ካለበት መጠን ከ7 እስከ 10 በመቶ ያክል ለመቀነስ ቃል የገባች ሲሆን፣ መንግሥት ግቡን ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጿል።

እ.አ.አ. እስከ 2035 ከጠቅላላው የኃይል ፍጆታዋ ከ30 በመቶውን ከጋዝ ወደ ታዳሽ የኃይል አማራጭ ለመቀየርም ቻይና ግብ አስቀምጣለች።

የንፋስ እና የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎቿን እ.አ.አ. በ2020 ከነበሩበት ከስድስት እጥፍ በላይ በማሳደግ በ2035 ወደ 3 ሺህ 600 ጊጋ ዋት ማሳደግ ሌላው የቻይና ግብ ነው።

የደን ልማቷን ከፍ በማድረግ የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ የሚያስችል ሥራም ጀምራለች።

የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን እና ታዳሽ ኃይል የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት አረንጓዴ ማኅበረሰብን ለመፍጠር ከፍተኛ በጀት መመደቧንም ይፋ አድርጋለች።

ግቡን ተግባራዊ ለማድረግም በኮሙኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ይሁንታ የተሰጠውን የመጀመሪያ አምስት ዓመታት ስትራቴጂ አውጥታ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምራለች።

በአሁኑ ጊዜ ቻይና በፀሐይ እና በውኃ ኃይል ማመንጫዎች አቅም የዓለማችን ግንባር ቀደም ስትሆን፣ በመጀመሪያው አምስት ዓመት ታዳሽ ኃይልን በእጥፍ በማሳደግ የድንጋይ ከሰል አጠቃቀምን እየቀነሱ መሄድ የሚያስችሉ አስገዳጅ ሕጎችን አውጥታለች።

መንግሥት እንደ ብረት እና ሲሚንቶ ያሉ ከባድ ኢንዱስትሪዎችን በሒደት እየቀነሰ እንደ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች፣ ባትሪዎች እና የፀሐይ ፓናሎች ያሉ አረንጓዴ ኢንዱስትሪዎችን በስፋት ለመገንባት ፖሊሲ አውጥቶም ወደ ሥራ እየገባ ነው።

ሌላው ብሔራዊ የልቀት ቅነሳ ማበረታቻ ስርዓት መተግበር ሲሆን፣ ይህም በሀገሪቱ የሚገኙ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች የካርቦን ልቀት መጠናቸውን እየቀነሱ በሄዱበት መጠን ማበረታቻ ክፍያዎች የሚያገኙበት ስርዓት ነው።

ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ላይ ዳተኛ በሆነበት በአሁኑ ወቅት፣ ይህ ቻይና በራሷ ላይ ወስና የጀመረችው ቁርጠኛ እንቅስቃሴ የፓሪስ ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ ተስፋ ሰጪ የተግባር እርምጃ እንደሆነም ሲጂቲኤን ዘግቧል።

 

በለሚ ታደሰ