ለኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር የሀገር ሕልውናን የመታደግ፣ የሀገራዊ ደኅንነትን የማረጋገጥ እና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የማስከበር ቁልፍ ስትራቴጂ ነው።
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት እና አብዛኛው ዜጋዋ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በዝናብ ጥገኝነት ላይ በቆመ ግብርና በምተዳደርባት ሀገር፣ የአፈር መሸርሸር እና የመሬት መራቆት ተራ የተፈጥሮ ክስተቶች አይደሉም፤ ይልቁንም የሕዝብን የምግብ ዋስትና የሚያናጉ፣ ማህበራዊ መረጋጋትን የሚፈትኑ የደህንነት ስጋቶች ናቸው።

በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ቶን ለም አፈር በጎርፍ እና በንፋስ እየተጠረገ መሄዱ የኢኮኖሚውን መሠረት የሚንድ በመሆኑ፣ ይህንን አውዳሚ ሂደት በአረንጓዴ ዐሻራ አማካኝነት ለመቀልበስ መነሣት የሀገርን ዘላቂ ሕልውና ከጥፋት የመታደግ የታሪክ ግዴታ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል።
ይህ መጠነ-ሰፊ የአረንጓዴ ልማት ንቅናቄ ከሀገር ውስጥ አልፎ ቀጣናዊ እና ጂኦፖለቲካዊ ፋይዳው እጅግ የጎላ ነው።
በተፈጥሮ መራቆት ምክንያት የሚከሰተውን የተፋሰሶች መድረቅ በመከላከል እና የከርሰ-ምድር ውኃን በከፍተኛ ሁኔታ በማበልጸግ ረገድ የአረንጓዴ ዐሻራ ሚና ወደር የለውም።
ይህ የውኃ ሀብት ጥበቃ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ለሚጋሩ የጎረቤት ሀገራት ጭምር የውኃ ደኅንነትን እና አስተማማኝነትን የሚያረጋግጥ ትልቅ ዋስትናም ነው።
በአፍሪካ ቀንድ እና በናይል ተፋሰስ አካባቢ የሚታየውን የውኃ እጥረት ስጋት በመቅረፍ፣ ሀገራት በውኃ ሀብት አጠቃቀም ዙሪያ ወደ ግጭት እና አለመግባባት ከማምራት ይልቅ በጋራ ልማት እና በትብብር ላይ የተመሠረተ ዲፕሎማሲ እንዲከተሉ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ልማት በቀጣናው ያለውን ሰላም እና ጂኦፖለቲካዊ መረጋጋት በቀጥታ የሚወስን የሰላም ስትራቴጂ ሆኖ ያገለግላል።
በተጨማሪም የሀገራችንን የማክሮ-ኢኮኖሚ መዋቅር ወደ ላቀ እና የማይበገር ደረጃ ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት ውስጥ፣ ይህ አረንጓዴ ኢኮኖሚ የራሱን ጉልህ ዐሻራ እያሳረፈ ይገኛል።
የአካባቢ ጥበቃ ሥራው የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ፣ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች በተለይም ደግሞ በማኅበረሰቡ ውስጥ በኢኮኖሚ ተጋላጭ ለሆኑት ወጣቶች እና ሴቶች ሰፊ የሥራ ዕድልን መፍጠር ችሏል።
ይህ ከችግኝ መኮትኮት እስከ ደን ጥበቃ እና ልማት የተዘረጋው የሥራ ዕድል፣ የዜጎችን ዕለታዊ ገቢ ከማሻሻሉም በላይ የሀገራዊ የምጣኔ-ሀብት መቋቋም አቅምን የሚገነባ ጠንካራ ምሰሶ ሆኗል።

በመሆኑም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር የአካባቢ ጥበቃን፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን እና የጂኦፖለቲካ መረጋጋትን በጋራ በማስተሳሰር የነገዋን የበለጸገች እና ሉዓላዊነቷ የተከበረ ኢትዮጵያን ለመገንባት የተነደፈ ሥልታዊ እና አርቆ አሳቢ የፖሊሲ ምላሽ ነው።
በበረከት ሽመልስ