Search

ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዓለምን ያስደነቁ ስኬቶችን አስመዝግባለች - ዲማ ኖጎ (ዶ/ር)

ዓርብ ሰኔ 12, 2018 56

 

ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በዲፕሎማሲው መድረክ ያጋጠሟትን ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች በጽናት በመቋቋም፣ ዓለምን ያስደነቁ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችላለች።

ሀገራችን ቀጠናዊ ትብብሯን በማሳደግ እና አህጉራዊ ሚናዋን ዳግም በማጠናከር ረገድ አዲስ የዲፕሎማሲ ታሪክ እየጻፈች ይገኛል።

በዲፕሎማሲው ዘርፍ ከአጎራባች ሀገራት ጋር የምታደርገው የሰላም ጥረትና የልማት ትብብር፣ በአፍሪካ መድረክ ላይ እያሳየች ያለችው ንቁ ተሳትፎ እና በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ውስጥ ያላት ስትራቴጂካዊ ቦታ ለዚህ ዋነኛ ማረጋገጫዎች ናቸው።

ሀገራችን በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ድርድር፣ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንዲሁም ታላላቅ ዓለም አቀፍ መድረኮችን በስኬት በማስተናገድ ረገድ ያሳየችው አፈጻጸም የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲዋን ያጠናከረ ሆኗል።

ይህ ስኬት ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት እና የፋይናንስ ተቋማትን በስፋት ለመሳብም ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (/) ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው በዚህ ጉዳይ ላይ ቆይታ አድርገዋል፡፡

እርሳቸው እንዳሉት ምክር ቤቱ የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ ባለፉት አምስት ዓመታት የተለያዩ ሕጎችን በማውጣት እና በማስፈጸም በኩል ከፍተኛ ኃላፊነት ተወጥቷል።

የወጡት ሕጎች እና የተከናወኑት የቁጥጥር ሥራዎችም የሀገራችንን ዘላቂ ጥቅም የሚያስከብሩ እና የሚጠብቁ መሆናቸውን የማረጋገጥ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል።

ከዚህ ባሻገር፣ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ፓርላማዊ ዲፕሎማሲን (Parliamentary Diplomacy) በተደራጀ መልኩ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ሰፊ ሥራዎች ተከናውነዋል።

በዚህም ፓርላማ ለፓርላማ እና ሕዝብ ለሕዝብ የሚደረጉ ግንኙነቶችን ከተለያዩ ሀገራት ምክር ቤቶች እና የወዳጅነት ቡድኖች ጋር በመፍጠር፣ የሁለትዮሽ እና የብዙኃን ግንኙነቶችን የማጠናከር ተግባራት በስኬት መከናወናቸውን ሰብሳቢው ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በስኬት ካከናወናቸው ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች መካከል ቀዳሚው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ መሆኑን ዶክተር ዲማ ገልጸዋል፡፡

ግድቡ በሚገነባበት ወቅት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከፍተኛ የሆነ የዲፕሎማሲ ጫና ያጋጠመ ቢሆንም፣ ሀገራችን በአንድ በኩል ዲፕሎማሲያዊ ድርድሩን በብቃት እየመራች በሌላ በኩል ደግሞ የግንባታ ሥራውን በተከታታይ ማከናወን መቻሏን አስታውሰዋል።

ለዚህም ማሳያ የሚሆነው፣ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ አጀንዳ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት መድረክ ላይ 13 ጊዜ ያህል መነሳቱ እና ለውይይት መቅረቡን ጠቅሰው፣ ወቅቱ ከፍተኛ ጫና እና ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ በሀገራችን ላይ ተጥሎ የነበረበት ከባድ ወቅት እንደነበር አስታውሰዋል።

በተያያዘም የኢትዮጵያን የባሕር የባሕር በር ጥያቄ እና ፍላጎት በተመለከተ ሀገራችን መብቷን ለማስከበር የሄደችበት መንገድ ሙሉ በሙሉ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድን የተከተለ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንድትሆን እና የኢኮኖሚ ጥቅሟ እንዲከበር ጥያቄዋን በተለያዩ ሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ አማራጮች ስታቀርብ መቆየቷን እና አሁንም ይህንንው መንገድ እየተከተለች መሆኑን አስገንዝበዋል።

በንፍታሌም እንግዳወርቅ