Search

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ገጽታ እየቀየረ ያለው የገጠር ኮሪደር ልማት

ዓርብ ሰኔ 12, 2018 65

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚያዊ እና የማኅበራዊ ልማት ሽግግር በአሁኑ ወቅት ታሪካዊ በሆነ አዲስ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የሀገራችን ከተሞች የተከናወነው የኮሪደር ልማት ከተሞቹን ከነበሩበት ያልተደራጀ የኑሮ ዘይቤ በማላቀቅ ረገድ ከፍተኛ ስኬት አስመዝግቧል።

ይሁን እንጂ የሀገራችንን ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ብልጽግና ለማረጋገጥ የከተማ ልማት ብቻውን በቂ ባለመሆኑ፣ 2017 . ጀምሮ ለገጠር ኮሪደር እና ዘመናዊ መንደሮች ልማትም ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በተደጋጋሚ እንደሚሉት፣ "የኢትዮጵያ ብልጽግና መሠረት አርሶ አደሩ ነው፤ አርሶ አደሩን ከጭቃ ቤት፣ ከጭስ እና ከኋላቀር የኑሮ ዘይቤ ወደ ዘመናዊ አኗኗር ሳናሸጋግር ስለ ሀገር ብልጽግና ማውራት አንችልም"

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽኑ አቋም ዛሬ ላይ የገጠሩን ማኅበረሰብ አኗኗር በዘላቂነት ለመቀየር ያለመ ትልቅ ሀገራዊ ንቅናቄ ሆኖ ወደ መሬት ወርዷል።

ሀገር መጋቢ እና የኢኮኖሚው መሠረት ሆኖ የኖረው የኢትዮጵያ አርሶ አደር፣ የእርሱ ኑሮ ግን ሳይለወጥ ለዘመናት ቆይቷል።

እናቶች በጭስ በታፈነ ኩሽና ሲሰቃዩ እንዲሁም ሰው እና እንስሳት በአንድ ጣሪያ ስር ሲኖሩ ማየት የተለመደ የአርሶ አደሩ የሕይወት ገጽታ ነበር።

አሁን ላይ መንግሥት የቀየሰው የገጠር ልማት ስትራቴጂ ግን ይህን የድህነት ቀንበር በመስበር አርሶ አደሩ ሰብዓዊ ክብር እና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ የሚጎናጸፍበትን መንገድ ከፍቷል።

በሀገራችን እየተስፋፉ ባሉ የገጠር ዘመናዊ መንደሮች፣ ጠባብ እና ፕላን የሌላቸው የጭቃ ቤቶች በአካባቢ ጥሬ ዕቃ በተገነቡ ሰፋፊ እና ዘመናዊ ቤቶች እየተተኩ ነው። ይህ ዓይነቱ የገጠር ትራንስፎርሜሽን በዓለም አቀፍ ደረጃም የተሞከረ እና ውጤት ያመጣ ነው።

ለምሳሌ ደቡብ ኮሪያ ሴማኡል ኡንዶንግ' በሚል 1970ዎቹ የጀመረችው የአዲስ መንደር ንቅናቄ ገጠርን በማዘመን እና የሀገሪቱን አርሶ አደር ከድህነት በማውጣት ኢኮኖሚያዊ ተዓምር መሥራት አስችሏታል።

ቻይናም በተመሳሳይ የገጠር ማነቃቂያ ስትራቴጂ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿን ከድህነት አውጥታለች።

ኢትዮጵያም እመርታ ያመጣውን ይህን ዓለም አቀፍ ተሞክሮ በሀገር በቀል ዕውቀት በመቀመር እየተገበረች ትገኛለች።

በሀገራችን እየተገነቡ ያሉት አዲሶቹ ዘመናዊ የገጠር ቤቶች የማገዶ ጭስን በንፁህ የፀሐይ (ሶላር) እና የባዮጋዝ ኃይል የተኩ ናቸው።

በነዚህ ዘመናዊ የገጠር ቤቶች የሚኖረው አርሶ አደር "ሌማት ትሩፋት" አማካኝነት በጓሮው ዶሮ፣ አትክልት፣ ማር እና የወተት ተዋጽኦ እንዲያመርት በመደረግ ላይ ይገኛል።

የአርሶ አደሩ የኑሮ ዘይቤ መዘመን አሁን ላይ በግቢው ትራክተር እና መኪና የሚያቆምበት የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ደረጃ ላይ እያደረሰው ነው።

በዚህ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ጉዞ የኦሮሚያ ክልል ተሞክሮ በልዩ ሁኔታ የሚነሳ ነው።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ "የአርሶ አደሩን ቤት ከመቀየር ጀምሮ የገቢ አቅሙን ማሳደግ ትልቁ የትግላችን አካል ነው" በማለት የጀመሩት ንቅናቄ ፍሬ እያፈራ ነው።

በክልሉ በርካታ አካባቢዎች የእናቶችን እንግልት ያስቀሩ፣ ከእንስሳት በረት የተለዩ እና በዘመናዊ መሠረተ ልማት የተደራጁ በርካታ ዘመናዊ የገጠር መንደሮች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።

ይህ የክልሉ ተሞክሮ አርሶ አደሩን በራሱ ቀዬ ወደ ባለሀብትነት የመቀየር ራዕይ በተግባር ሊሳካ የሚችል መሆኑን ያረጋገጠ ነው።

ይህንኑ የልማት ፖሊሲ በማስፋት በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በሐረሪ እና በሌለችም የሀገራችን ክፍሎች ምርታማነት በእጥፍ እያደገ ይገኛል።

ይህ ሀገር አቀፍ የገጠር ኮሪደር እና የዘመናዊ መንደሮች ልማት የገጠር ከተማ ፍልሰትን በመግታት ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ አለው።

የገጠር ቀበሌዎች እንደ ከተማ የኤሌክትሪክ፣ የንፁህ ውኃ፣ የመንገድ እና የኢንተርኔት መሠረተ ልማት እንዲሟላላቸው በመደረጉ፣ አርሶ አደሩ በገዛ ቀዬው ዘመናዊ ሕይወት መምራት ችሏል።

ይህ አዲስ የፖሊሲ አቅጣጫ ይበልጥ ተጠናክሮ ሲቀጥል፣ የሀገራችን አርሶ አደር ምርቱን ለዓለም ገበያ የሚያቀርብ ባለሀብት ከመሆኑም ባሻገር፣ ኢትዮጵያ በምግብ ሉዓላዊነት ራሷን የቻለች የብልጽግና ተምሳሌት እንድትሆን ጽኑ መሠረት ይጥላል።

በለሚ ታደሰ