የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ አሁን የደረሰበት የድል ምዕራፍ እንዲደርስ በብዙ ፈተናዎች እና ውጣ ውረዶች ውስጥ ማለፍ የግድ ነበር።
የዚህ ስምንት ዓመት የዲፕሎማሲ ጉዞ አንዱ እና ትልቁ ማሳያ ኢትዮጵያ በውኃ ሀብቷ ላይ የነበራትን የተነጠቀ መብት ለማስመለስ ያደረገችው መራራ ትግል እና ያስመዘገበችው ታሪካዊ የውኃ ዲፕሎማሲ ድል ነው።
ለዘመናት የቆየውን የግብጽን የውኃ የበላይነት ጫና ለመስበር የተደረገው ተጋድሎ እጅግ ፈታኝ ነበር።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማደናቀፍ ጉዳዩ በ2020 እና 2021 እ.አ.አ ወደ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ ተወስዶ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ እና የኃያላን ሀገራት ጫና ሲደረግባት ቆይቷል።
ሆኖም ኢትዮጵያ "ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ" በሚል ጽኑ አቋም የድርድሩን አቅጣጫ በመቆጣጠር ግድቡን በስኬት ማጠናቀቅ ችላለች።
ከዚህም የላቀው የዲፕሎማሲ ስኬት፣ የ1929 እና የ1959ኙን አግላይ የቅኝ ግዛት ውሎችን በማስወገድ የዓባይ ወንዝ የተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ወደ ሥራ እንዲገባ ማድረጓ ነው።
ይህ ስምምነት በኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳ፣ ብሩንዲ እና ደቡብ ሱዳን ፀድቆ የናይል ተፋሰስ ኮሚሽንን እውን በማድረግ ኢትዮጵያን የውኃ ዲፕሎማሲ አሸናፊ አድርጓታል።
ሌላው ኢትዮጵያን ወደ ልዕልና ያወጣው ስትራቴጂያዊ ለውጥ፣ ከአንድ ወገን የኃይል ጥገኝነት ወጥታ ወደ ባለብዙ ዋልታ አሰላለፍ መሸጋገሯ ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በአብዛኛው በአንድ የኃይል ጎራ ላይ ያዘነበለ እና የዓለም አቀፍ የፀረ-ሽብር ዘመቻ ውክልና ሚናን የተጫነ ነበር።
በአዲሱ ዲፕሎማሲ ግን፣ ኢትዮጵያ የ"ስትራቴጂያዊ ማመጣጠን" እና "የባለብዙ አሰላለፍ" ፖሊሲን በመከተል ጂኦ-ፖለቲካዊ ነፃነቷን አረጋግጣለች።
ሀገራችን ራሷን ለየትኛውም የኃይል ጎራ አሳልፋ ሳትሰጥ፣ ከቻይና እና ሩሲያ ጋር ያላትን ስትራቴጂያዊ አጋርነት በማጠናከር የውጭ ጥገኝነትን ስትቀንስ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ያላትን የኢኮኖሚ እና የደኅንነት ትብብር አጎልብታለች።
ከመካከለኛው ምሥራቅ አዳጊ ኢኮኖሚዎች ጋርም (እንደ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና ቱርክ) ከፍተኛ የሆነ የኢንቨስትመንት እና የሥራ ሥምሪት ትብብሮችን ፈጥራለች።

ይህ ሚዛናዊ እና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ መድረክ ቁልፍ ተዋናይ እንድትሆን አድርጓታል።
አዳጊ እና ግዙፍ ኢኮኖሚዎችን ያቀፈውን ታላቁን የብሪክስ ስብስብ እ.አ.አ ጥር 1 ቀን 2024 በይፋ መቀላቀሏ፣ ከ40 በላይ ሀገራት በጠየቁበት ፉክክር ውስጥ ተመራጭ መሆን መቻሏ፣ ሀገራችን ያላትን ዓለም አቀፋዊ ተደማጭነት እና የድርድር አቅም አረጋግጧል።
በተጨማሪም የባሕር በር የሕልውና ጥያቄን ከአይነገሬነት አውጥታ በዓለም አቀፍ መድረክ በማምጣት ፍትሐዊ መፍትሔ ለማግኘት በድፍረት እየሠራች ትገኛለች።
ዲፕሎማሲው ለኢኮኖሚውም ያበረከተው አስተዋፅኦ የላቀ ነበር፤ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን 4 ቢሊዮን ዶላር ማድረስ፣ የወጪ ንግድን ወደ 8.3 ቢሊዮን ዶላር ማሳደግ፣ እና ከ500 ሺህ በላይ በችግር ውስጥ የነበሩ ዜጎችን በክብር መመለስ መቻሉ የዚሁ ዜጋ-ተኮር ዲፕሎማሲ ፍሬዎች ናቸው።
በአንድ ዓመት ብቻ ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በማስተናገድ እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራ ስኬቷ የCOP32 አዘጋጅነትን እና ዓለም አቀፍ የFAO ሽልማቶችን እንድታገኝ አስችሏታል።
በአጠቃላይ ሲታይ፣ ያለፉት ስምንት ዓመታት የዲፕሎማሲ ጉዞ ኢትዮጵያን ከተረጂነት፣ ከጥገኝነት እና ከከበባ ሥነ-ልቦና ያላቀቀ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።

በውስጥ አቅም እና በተግባር በተደገፈ ፖሊሲ፣ ሉዓላዊ ጥቅሟን በማስከበር በዓለም አቀፍ መድረክ የራሷን ክብር መልሳለች። ኢትዮጵያን የሚመጥነው ዲፕሎማሲ ይህ ነው! ከኩስመና ወጥቶ ልዕልናን የሚያረጋግጥ፣ የውኃ እና የባሕር በር መብትን በፅናት የሚያስከብር እና የጋራ ብልፅግናን የሚያውጅ ተግባራዊ ስትራቴጂ።
ይህ የተጀመረው ሚዛናዊ እና ብሔራዊ ጥቅምን ያማከለ የዲፕሎማሲ መስመር በተቋማዊ ጥንካሬ ሲቀጥል፣ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የጂኦ-ስትራቴጂያዊ ልዕልና በዘላቂነት እንደሚያረጋግጥ ጥርጥር የለውም።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ