በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የሚነሱ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ክርክሮች ሁሉ ማጠንጠኛቸውን የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ማድረጋቸው አልቀረም።
በዚህ ታላቅ ዓለም አቀፋዊ ፈተና ውስጥ ግን ፍጹም ፍትሃዊነት የጎደለው እውነታ ይስተዋላል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ሀገራት ለከባቢ አየር መበከል እና ለሙቀት መጨመር ከፍተኛውን ድርሻ ቢይዙም፣ የዚህ አውዳሚ የተፈጥሮ መዛባት ቀጥተኛ ሰለባ እና ተጎጂ እየሆኑ ያሉት ግን አነስተኛ የካርቦን ልቀት ያላቸው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አዳጊ ሀገራት መሆናቸው ነው።
ይህ ዓይነቱ የተዛባ ሚዛን ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን እና የተስፋ ቃላትን በተደጋጋሚ ሲፈታተን የቆየ ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን በቅሬታ እና በይግባኝ ላይ ብቻ አልተወሰነችም።
ይልቁንም በአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄዋ አማካኝነት "ተግባራዊ የአየር ንብረት ፍትህ" ምን ማለት እንደሆነ በተጨባጭ ማሳየት ችላለች።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የሚገቡ የቃላት ቃልኪዳኖችን በመሻገር፣ በተግባር በአጭር ጊዜ ውስጥ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል እና ወደ 300 ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ ካርቦን ዳይኦክሳይድን በመምጠጥ ረገድ ውጤታማ ሆናለች፡፡
ይህም የኢትዮጵያ አዳጊ ሀገራት የበለጸጉትን ሳይጠብቁ የአየር ንብረት መፍትሔ አቅራቢ መሆን እንደሚችሉ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተግባር ያሳየችበት ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ ነው።

ይህ ተግባራዊ ምላሽ ደግሞ የኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ ድርድር እና የአየር ንብረት ፋይናንስ አቅም ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮታል።
ኢትዮጵያ እንደ ግሎባል ኢንቫይሮንመንት ፋሲሊቲ (GEF) እና የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም (UNEP) ካሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ የዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በስትራቴጂክ ደረጃ በጋራ በመሥራት ላይ ትገኛለች።
በአረንጓዴ ዐሻራ ዙሪያ የምታገኘው መጠነ-ሰፊ የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍም፣ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮጀክቶችን በገንዘብ ከመደገፍ ባለፈ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላትን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ የድርድር አቅም እጅግ ከፍ አድርጎታል።
አረንጓዴ ዐሻራ አሁን ላይ የአፈር መሸርሸርን መከላከያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ጠረጴዛዎች ዙሪያ ሀገራዊ ጥቅምን ለማስከበር እና ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ የሚያስችል ጠንካራ የዲፕሎማሲ መደራደሪያ አማራጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
የዚህ ስኬታማ ጉዞ ትልቁ ዲፕሎማሲያዊ ማሳያ እና የድል አክሊል ደግሞ ኢትዮጵያ እአአ በ2027 የሚካሄደውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ (COP32) በአስተናጋጅነት እንድትመራ መመረጧ ነው።
ይህ ኮንፈረንስ የዓለም መሪዎች፣ ሳይንቲስቶች እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ተሰባስበው የዓለምን ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚወስኑበት ታላቅ መድረክ ነው።
ኢትዮጵያ ይህንን ታሪካዊ ኮንፈረንስ እንድትመራ መመረጧ በአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄዋ ያካበተችውን ውጤት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በይፋ ያወቀላት መሆኑን ያረጋግጣል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የራሷን የአረንጓዴ ዐሻራ ተሞክሮ እንደ ስኬታማ መነሻ በመጠቀም፣ መላውን የአፍሪካ አህጉር በፋይናንስ፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በአረንጓዴ ሽግግር ዙሪያ በጋራ አቋም እንድትመራ ትልቅ የዲፕሎማሲ በር ይከፍትላታል።

አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ በከፍተኛ ሁኔታ የምትጎዳ ቢሆንም ድምጿ ብዙ ጊዜ ሳይሰማ የመቅረቱን ታሪክ ለመቀየር፣ ኢትዮጵያ የአህጉሪቱን የጋራ ድምጽ ለዓለም በማስተጋባት ረገድ ቁልፍ መሪ ሆና እንድትወጣም ያደርጋታል።
ስለሆነም የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ አሁን ላይ የአገር ውስጥ አካባቢን የመጠበቅ ወይም የችግኝ ተከላ ስራ ብቻ መሆኑ አብቅቷል።
ይልቁንም ለኢትዮጵያ ዘላቂ ህልውናዋን የምታረጋግጥበት፣ የምግብ ዋስትናዋን የምታስጠብቅበት እና የቀጠናዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ሚናዋን የምታጎለብትበት ታላቅ የዲፕሎማሲ መሳሪያ ሆኗል።
ለተቀረው ዓለም ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት የግድ የበለጸገ ሀገር መሆን እንደማያስፈልግ እና አዳጊ ሀገራት ጭምር በራሳቸው ቁርጠኝነትና አቅም የዓለምን ስነ-ምህዳር ለመታደግ እንዴት በተግባር ግንባር ቀደም መሪ መሆን እንደሚችሉ ያሳየ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ አዲስና ተስፋ ሰጪ መልክ ነው።
በበረከት ሽመልስ