Search

የአረንጓዴ ዐሻራ ፡ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገጽታ የለወጠው ብሔራዊ ንቅናቄ

ዓርብ ሰኔ 12, 2018 102

 

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ ለረጅም ዓመታት በታሪካዊ ስፍራዎች እና በባህላዊ እሴቶች ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ጥገኝነት ነበረበት።

ይህ የቱሪዝም ምርት ውስንነት የጎብኚዎችን የመቆያ ጊዜ የሚያሳጥር እና ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚገድብ ዋና ፈተና ሆኖ ቆይቷል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር ይህንን መዋቅራዊ ክፍተት በመቅረፍ፣ አዳዲስ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሮአዊ መስህቦችን ወደ ገበያ በማስገባት የሀገራችንን የቱሪዝም ምርት በከፍተኛ ደረጃ እንዲበራከት እና እንዲዘምን እያደረገ ይገኛል።

ይህ ብሔራዊ ንቅናቄ የቱሪስት ፍሰትን በማብዛት ረገድ ያመጣው ትልቁ ለውጥ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የቱሪዝም ገበያ የምትታወቅበትን መልክ እና ምስል ሙሉ በሙሉ መቀየሩ ነው።

ቀደም ሲል ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ለታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናት፣ ጥንታዊ መስጂዶች እና ለቅርሶች ጉብኝት ብቻ ነበር።

አሁን ላይ ግን በአረንጓዴ ዐሻራ ማዕቀፍ የለሙት ግዙፍ ፕሮጀክቶች አነቃቂ እና ተመራጭ የቱሪዝም አማራጮች ሆነዋል።

በተለይም ላለፉት ዓመታት ከተተከሉት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞች ባሻገር፣ እንደ "ገበታ ለሀገር" እና "ገበታ ለትውልድ" ባሉ ሀገራዊ የልማት ውጥኖች አማካኝነት የለሙት የጎርጎራ፣ የወንጪ፣ የሀላላ ኬላ እና የጨበራ ጮርጮራ ግዙፍ የኢኮ-ቱሪዝም መዳረሻዎች የዘርፉን አቅም በከፍተኛ ደረጃ አሳድገውታል።

የእነዚህ ሥነ-ምህዳርን መሰረት ያደረጉ አማራጮች መበራከትም ሀገራችን የተለያየ ፍላጎት ያላቸውን ቱሪስቶችን እና ሀገር ጎብኚዎችን በስፋት እንድትስብ ትልቅ አቅም ፈጥሮላታል።

በተለይም ዋና ከተማችን አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና በመሆኗ ለስብሰባ እና ለኮንፈረንስ ቱሪዝም የሚመጡ ዓለም አቀፍ እንግዶች ቁጥር ከፍተኛ ነው።

ከዚህ ቀደም እነዚህ ዲፕሎማቶች እና ተጓዦች ከስብሰባ ሰዓት ውጭ የሚያሳልፉባቸው የአረንጓዴ መዝናኛ ስፍራዎች እጥረት የነበረባቸው ሲሆን፣ በአሁን ወቅት ግን ከተማዋን ያስዋበው የአረንጓዴ ዐሻራ፣ ሰፊ የኮሪደር ልማት እና የወንዝ ዳርቻዎች ማልማት ፕሮጀክቶች ይህን ችግር ሙሉ በሙሉ ቀርፈውታል።

የአረንጓዴ ዐሻራ ያስዋባቸው እንደ አንድነት፣ ወዳጅነት እና እንጦጦ ፓርኮች ያሉ ዘመናዊ መዳረሻዎች ይህንን የቆይታ ክፍተት በብቃት ሞልተውታል።

የከተማዋ አየር ንብረት ይበልጥ ማራኪ እየሆነ መምጣቱም የእንግዶችን ቆይታ እያራዘመው ነው።

በዚህም የኮንፈረንስ ቱሪዝም ከአረንጓዴ መዝናኛ ጋር በጥብቅ መተሳሰሩ እንግዶች በሀገር ውስጥ ተጨማሪ ቀናትን እንዲያሳልፉ በማድረግ የቱሪስቶችን ወጪ ከፍ እንዲል እና የሀገራችን የውጭ ምንዛሬ ግኝት እንዲያድግ እያደረገ ይገኛል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር የቱሪዝም ምርትን ብዝኃነት በማረጋገጥ ረገድ ያበረከተው አስተዋፅኦ፣ የሀገራችንን የቱሪዝም ኢኮኖሚ ከአንድ ወገን ጥገኝነት ያላቀቀ እና ወደ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ያሸጋገረ ስትራቴጂካዊ ስኬት ነው።

በሔዋን ጌታቸው