በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሰላምን ለማምጣት በተሠራው የተቀናጀ ሥራ ውጤት እየመጣ መሆኑን የዞኑ ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አንተነህ ታደሰ ገልጸዋል።
በዞኑ በተደረገው ሁሉን አቀፍ የተቀናጀ ጥረት በተያዘው በጀት ዓመት በሺህዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የመንግሥትን የሰላም አማራጭ ተቀብለው መግባታቸውንም ነው ያስታወቁት።
የሰላም አማራጭን ከተቀበሉት ታጣቂዎች መካከል አብዛኛዎቹ የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀላቸውን ተናግረዋል።

ከሥልጠናው በኋላም ወደ ነበሩበት ሥራ የመመለስ፣ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን የመፍጠር እና የመቋቋሚያ ድጋፍ የማመቻቸት ሥራ በልዩ ትኩረት እየተሠራበት ይገኛል ነው ያሉት።
አሁን ላይ የዞኑ የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱንም ገልጸው፣ ለዚህም ሕዝቡ ለዘላቂ ሰላም ያለው ቁርጠኝነት፣ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪን ተቀብለው መመለሳቸው እና አንዳንዶቹም ከተሰጣቸው የተሃድሶ ሥልጠና በኋላ የፀጥታ መዋቅሩን ተቀላቅለው ሰላምን ለማስከበር እየሠሩ መሆናቸው ነው ብለዋል።

አሁንም የቀሩት ታጣቂዎች ግጭት አውዳሚ መሆኑን በመገንዘብ ሰላማዊ መንገድን መርጠው እንዲመለሱ ጥሪ ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል።
የተገኘው አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ማኅበረሰቡም በጫካ ያሉትን ታጣቂዎች በመምከር ወደ ሰላም እንዲመለሱ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል።